በአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ውድመት የደረሰባቸውን የውሃና መብራት መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በጥናት የተደገፈ ማስተካከያ ይደረጋል

61

ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ውድመት የደረሰባቸውን የውሃና መብራት መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት መልሶ ለመገንባት በጥናት ላይ የተመሰረተ ማስተካከያ ይደረጋል” ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለጹ። 

ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የኢንዳስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋሞቻቸው ጋር በመተባበር በአሸባሪው በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ሰብዓዊ ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት ነው።

መስሪያ ቤቶቹ በድምሩ ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ሰብዓዊ ድጋፍ ለአፋር ክልል መንግስት አስረክበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂኔር ሃብታሙ ኢተፋ፥ አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል በገባባቸው የአማራና አፋር ክልሎች መሰረተ ልማቶችን በማውደም እና ንጹኃን ዜጎችን በጥይት ደብድቦ ከመግደል ባሻገር እናቶችና ህፃናትን በማስራብ ዜጎች እንዲጎዱ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

ይህ አሸባሪ ቡድን በአፋር ክልል የፈጸመውን የወረራ ድርጊት የአፋር ህዝብ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ተቀናጅቶ መመከቱን አስታውሰዋል።

የተሸነፈው ሽብርተኛ ኃይል የንጹኃን ዜጎችን ተጠቃሚነት ለመጉዳት የውሃና የመብራት መሰረተ ልማቶችን  በማውደም የጣለውን ጠባሳ ለመቀልበስ ተቋማቸው በጥናት ላይ የተመሰረተ ማስተካከያ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀደመ ቀዬአቸው ተመልሰው ኑሯቸውን እንዲጀምሩ ለማገዝ ከዚህ ቀደም ካደረገው የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ በተጨማሪ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ብርሃኑ ሰርጃቦ፥ አሸባሪው ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች ሰብዓዊ ቀውስ ማድረሱን አስታውሰው፤ ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚልም የኢንዳስትሪ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማቱ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ድጋፉም ለአፋር ክልልና ኮምቦልቻ አካባቢ ለሚገኙ ወገኖች እንዲደርስ የታሰበ መሆኑን አመላክተዋል።

የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት ሃጂ አወል አርባ፥ ተቋማቱ በሽብርተኛው ወራሪ ኃይል ተፈናቅለው ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲውል በማሰብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

አሸባሪው የህወሃት የጥፋት ቡድን የኢትዮጵያ እስትንፋስ የሆነችውን የሚሌ ኮሪደር በቀላሉ በመቆጣጠር ለድርድር እንቀርባለን ብለው ያጩት የአፋር ምድር መቃብራቸው እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

የሽብርተኛው ወራሪ ኃይል በአፋር ክልል ጦርነት በከፈተባቸው ሁሉም ግንባሮች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበት መደምሰሱንም አረጋግጠዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም