ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪው ቡድን የጥፋት ድርጊት በማውገዝ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ

219

ጂንካ፣ ታህሳስ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመውን የጥፋት ድርጊት በማውገዝ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ።

አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር  ክልሎች በእናቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመውን ግፍና በደል የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ተካሂዷል።

ሰልፈኞቹ አሸባሪው ቡድን የፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተቀባይነት የሌለው ከባድ የሥነልቡናና የአካል ጉዳት ያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አለም ፀሐይ ሻሆ በሰጡት አስተያየት፤ አሸባሪው ህወሓት ሴቶችና ህፃናት ላይ የፈጸማቸው ድርጊቶች ከባህልና እምነት አንፃር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ድምጻቸውን ለማሰማት በሰልፉ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሰላምነሽ ልንገርህ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን በንጹሃን ላይ የፈፀመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ኮንነዋል።

ቡድኑ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያወደመው ሀብትና ንብረትም የጭካኔ ጥግ ያሳየ ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ቡድን የሚፈፅመውን ድርጊት በማውገዝ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም እንዲቆም የጠየቁት ደግሞ ሌላዋ የሰልፉ ተሳታፊ  ወይዘሮ እቴቴ አያሌው ናቸው።

የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ምህረት በላይ፤  አሸባሪው ህወሓት የፈጸማቸው ወንጀሎች በትውልዱ የማይረሳና አስነዋሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጊቱን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ የሽብር ቡድኑን ሴራ ማጋለጥና ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከመንግሥት ጎን በመሆን የአሸባሪው ቡድን የጥፋት ድርጊቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቆም ይኖርብናል ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልል የሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ወይዘሮ ነኢማ ሙኒር ናቸው።