ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻው እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ደጀንነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

136

ጋምቤላ፣ ታህሳስ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻው እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ደጀንነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ አስገነዘቡ።

የጋምቤላ ክልል የሴት አደረጃጀቶችና ሴት ተማሪዎች አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

በሰልፉ ላይ የተገኙት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት በአሸባሪው ህወሓትና በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጥምረት የተደቀነውን አደጋ ለመመከት በሁሉም ግንባሮች እየተደረገ ያለውን ብርቱ ትግል መደገፍ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሀገር ላይ የተቃጣውን ወረራ፣ የኢኮኖሚያዊና የዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመቀልበስ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በየአውደ ግንባሩ እያደረጉት ባለው ተጋድሎ በርካታ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ሴቶች የትግሉ አካል በመሆን ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ፣ ለሰራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ደም በመለገስና በሌሎችም አውደ ግንባሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸማቸው ወረራዎች በንጹሃን እናቶች፣ ታዳጊ ሴቶች፣ ህፃናትና አረጋውያን ላይ ዘግናኝ ግፍ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

ይህንን ለመቀልበስ የተጀመረው ዘመቻ በስኬት እስኪጠናቀቅ ሴቶች የጀመሩትን ሁለንተናዊ ትግል አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ወይዘሮ ዳግማዊት አስገንዝበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ አጁሉ በበኩላቸው የህወሓት የሽብር ቡድን በአፋርና በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት ላይ ያደረው ጥፋት ሊዘነጋ የማይችል ጠባሳ መሆኑን ገልጸዋል።

በሴቶች፣ በህፃናትና በማህበራዊ ተቋማት ላይ ያደረሰው ጉዳት የአሸባሪነት ድርጊቱን በገሃድ ያሳየ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለህልውና ዘመቻው ስኬት የክልሉ መንግስት ሁለንተናዊ ደጀንነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በሰው አዕምሮ የማይታሰብ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት በአፋርና በአማራ ክልል እናቶቻችና ህጻናት ላይ መፈጸሙን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ሴቶችና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ክርሚስ ሌሮ ናቸው።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ተቋማት የአሸባሪውን ህወሓት የሽብር ተግባር አይተው እንዳላዩ ማለፋቸው ለአሸባሪው ህወሓት ያላቸውን ውግንና የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎችም አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈጸማቸውን ፆታዊ ጥቃትና ጭፍጨፋ አውግዘዋል።

የህልውና ዘመቻውን በማገዝ የአሸባሪውን ህወሓት ሴራ ለማክሸፍ የተቻለቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።  

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም