የአሸባሪዎቹን ህወሃት እና ሸኔ የጭካኔ ድርጊት ለማስቆም እንታገላለን

94

ሐረር፣ ታህሳስ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ በሴቶች እና በህፃናት ላይ እያደረሱት ያለውን የጭካኔ ድርጊት ለማስቆም ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፈው እንደሚታገሉ የሐረሪ ክልል ሴቶች ዛሬ ባካሄዱት ሰልፍ አስታወቁ።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ኢፍቱ ተስፋዬ እንዳሉት፤ አሸባሪዎቹ  ሴቶች፣ ህጻናትንና  የመለኮሱ እናቶችን  ጭምር የሚደፍሩ ሰብአዊ ባህሪ የሌላቸው  አረመኔዎች ናቸው።

ይህንን የጭካኔ ተግባር መላው የአለም ሊያወግዘው እንደሚገባ አመልክተው፤ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጠልቃ ከመግባትም መቆጠብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

አሸባሪዎቹ  የሚፈጽሙትን ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ለማስቆም ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፈው ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን በሰው ልጅ ላይ ያደረሰው ሰቆቃና ግፍ የጭካኔውን ጥግ ያሳየ ነው ያሉት ወይዘሮ ሰናይት ወንደሰን ናቸው።

የአሸባሪውን ህወሃት  የጭካኔ ተግባር ለማስቆም በሚደረገው ትግል ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ  መሆናቸውን ገልጸው፤ ሰራዊቱን የመደገፍ ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

ወይዘሮ ፈቲያ በከር በበኩላቸው፤ በሴቶች፣ ህጻናት እና አረጋውያን ላይ ግፍ እየሰሩ እና ህዝብን እያሳዘኑ የሚገኙትን አሸባሪዎቹ  ሸኔ እና ህወሃት በተባበረ ክንድ ልንታገላቸው ይገባል ብለዋል።

እኛም ሴቶች የተጎጂዎቹ አካል በመሆናችን ድርጊቱን በጋራ እንታገለዋለን ሲሉም ገልጸዋል።

የሐረሪ ክልል  ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ደሊላ ዩሱፍ  ባደረጉት ንግግር፤ “አሸባሪዎቹ በሴቶች እና ህፃናት ላይ ከፍተኛ የሆነ ኢሰብአዊ ድርጊት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል።

በሀገሪቱና ዜጎች ላይ እያደረሰ የሚገኘው ውድመትና ጥቃት ቡድኑን ለመመከት  ይበልጥ የሚያጀግነን እንጂ ወደ ኋላ የሚመልሰን  አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ህዝቡ አሸባሪው  በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ማውገዝና ቡድኑን ለመቅጣት እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊትን  እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ኢንጅነር ህይወት ሞሲሳ በበኩላቸው፤ ሴቶች ሀገርን ለማዳን ለተሰለፈው ሰራዊት ሁለገብ ድጋፍ በማድረግ አለኝታነታቸውን እያሳዩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሴቶች የሰራዊቱ ደጀን እንደመሆናቸው በቀጣይም የስንቅ ዝግጅት፣ የዘማች ቤተሰብን የመደገፍ፣ ደም የመለገስ እና በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ልማቱን በማጠናከር ግንባር ቀደምነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው  አሳስበዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም