የጀግናውን ነፍስ የታደገችው ወጣት

246

ታህሳስ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህልውና ዘመቻውን ጥሪ በመቀበል ስልጠና ወስዳለች፣ ሰርጎ ገቦችን በመከላከል የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ የመጠበቅ ተልዕኮ ተሰጥቷት በትውልድ ቀዬዋ ኮምቦልቻ ከተማ ግዳጇን ተወጥታለች።

ወጣት እስከዳር እሸቱ “ሀገር ከሌለ ምንም የለም” በሚል ሀሳብ የህልውና ዘመቻውን የተቀላቀለችው የምትተዳደርበትን የምግብ ቤት ስራ አቋርጣ ነው።

የአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ወደ አማራ ክልል ሲገባ የመጀመሪያ ግቡ አማራን ማዋረድና አንገት ማስደፋት፣ ሀብትና ንብረቱን በመዝረፍና በማውደም ቅስሙን መስበር ነው፡፡

በጨማሪም አሸባሪ ቡድኑ ንጹሃንን ያለርህራሄ በመጨፍጨፍ የጭካኔውን ጥግ አሳይቷል።

ወጣት እስከዳር የሽብር ቡድኑ የጥቃት ሰለባ ላለመሆን እግራቸው ወደ መራቸው የሚሸሹ ነዋሪዎችን ወደ ቤቷ እየወሰደች በነበረበት ጊዜ በአንዲት ጥሻ ውስጥ በጥይት ተመትቶ የሲቃ ድምፅ የሚያወጣ ሰው ትሰማለች።

የተፈናቃዮችን እቃ እንደያዘች በአካባቢው ድንገት ወደ ሰማችው ድምጽ ትጠጋለች።

ሰውየው የመከላከያ ሰራዊት አባል እንደሆነና በተኩስ ልውውጥ እግሩ ተመትቶ አጥንቱ በመሰበሩ መውደቁን አረጋገጠች።

ወደ ቤቷ በመውሰድም በጓሮ ደብቃ መንከባከብ ጀመረች።

አጥንቱ ተሰብሮ ስጋው የቀረውን የመከላከያ ሰራዊት አባል ቁስል በማጠብና በመንከባከብ ህይወቱን ታድጋዋለች።

አሸባሪ ቡድኑ የህክምና ተቋማትንና መድሃኒት ቤቶችን  ማውደሙ ደግም ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ትናገራለች፡፡

በዚህም በአካባቢዋ የሚኖር የወጌሻ ባለሙያ ወደ ቤቷ በመውሰድም ለወታደሩ እርዳታ እንዲሰጠው ያደረገች ሲሆን፤ የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ኃይሎች “ወታደር ቤታችሁ አታስገቡ፤ ይህንን ካደረጋችሁ እንገላችኋላን” በማለት ያስፈራራቸው ስለነበር ሁኔታውን እጅግ ፈታኝ አድርጎት ነበር ትላለች፡፡

“እግዚአብሔርም ፈቅዶ ወታደሩ ድኖ ሰራዊቱን ተቀላቅሏል” በማለት የነበረውን ሁኔታ ገልጻዋለች።

ወጣት እስከዳር በእርሷ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ሳያስፈራት የኢትዮጵያ ጠባቂ የሆነ የአንድ ወታደር ህይወት አድናለች።

የወጣቷ ጎረቤቶች “መልካምነቷ እስከ ህይወት መስዋዕትነት የሚያደርስ ነው፤ ለማድረግ ሳይሆን ለማሰብ የሚከብድ ጀግንነት ፈጽማለች” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

መልካምነት የወጣቷ የሰርክ ተግባር መሆኑንም እንዲሁ፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።