የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

134

ታህሳስ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ።

ስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የረቂቅ አዋጁን መነሻ፣ አስፈላጊነት፣ የያዛቸውን ድንጋጌዎችና ሌሎች ተጨማሪ ሃሳቦች በተመለከተ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በልሂቃን መካከል የሚስተዋለውን ልዩነትና አለመግባባት በማስተካከል ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ምክክሩን የሚመራ አካል በህግ ማቋቋም በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

የአዋጁ መዘጋጀት በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃን ተቀራራቢና ለአገራዊ አንድነት ገንቢ የሆነ አቋም እንዲይዙ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የኮሚሽኑን ገለልተኝነት ለማረጋገጥ በረቂቅ አዋጁ የተለያዩ ድንጋጌዎች መካተታቸውን ጠቅሰው የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ የስራ ዘመኑ 3 አመት ሲሆን ስራው ካልተጠናቀቀ በምክር ቤቱ ሊራዘም እንደሚችል ተቀምጧል ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ ምክክር የሚደረግበት ተቋም ለመፍጠር መሰራቱን ታሪካዊ መሆኑን አንስተው ቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር ማየት ያለበትን ሃሳብም ጠቅሰዋል።

ምክር ቤቱ የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ በጥልቀት ተወያይቶ የተነሱ ሃሳቦችን ጨምሮ በዝርዝር እንዲያየው ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው የመንግስትና የግል  ሰራተኞች ጡረታ ለመደንገግ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም