በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ ኢንዱስትሪዎች እንዲያገግሙ መንግስት በተለየ መልኩ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል

166

ታህሳስ 7/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ ኢንዱስትሪዎች እንዲያገግሙ መንግስት በተለየ መልኩ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሸባሪ ቡድኑ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ኮሪደር በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ያደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን ተሰማርቶ እንደነበር ገልጸዋል።

በጥናቱ መሰረትም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ በኬሚካልና ኮንስትራከሽን፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በአግሮ ፕሮሰሴንግና በቆዳ ውጤቶች የተሰማሩ 40 ኢንዱስትሪዎች የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል።

በተለይም አካባቢውን ይበልጥ ይጠቅማሉ በሚል በታሰቡ ኢንዱስትሪዎች ላይ የተለዬ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ታሪክ ይቅር በማይለውና በኢትዮጵያ ላይ ያላውን ጥላቻ ባሳየበት በዚህ ውድመት በባለሃብቶች እና በሰራተኞች ላይ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማሰማራት ፋብሪካዎች ላይ ከፈጸመው ዘረፋና ውድመት ባሻገር ፋብሪካዎቹን በጦር ካምፕነትና ምሽግነት ተጠቅሟል ብለዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የዘረፋቸውን ንብረቶች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታርጋ በለጠፉ መኪኖች ማመላለሱንና ኀብረተሰብን አስገድዶ ወደ ፋብሪካዎች በማስገባት እነርሱ የዘረፉ አስመስሎ በካሜራ መቅረጹን ተናግረዋል፡፡

የዘረፏቸውን ተቋማት ሰነዶችን የማጥፋት ሌላው በአሸባሪ ቡድኑ የተፈጸመ ውድመት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ጉዳት በደረሰባቸው በ40 ኢንዱስትሪዎች በተደረገው ጥናት ስምንቱ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው በመሆኑ በአጭር ጊዜ ወደስራ መመለስ እንደማይችሉም ነው ያብራሩት።

ከነዚሀም መካከል ኢትፉድ ማኑፋክቸሪንግ፣ ጎሽ ሜዳ ቧንቧና ፕላስቲክ ልማት ማህበር፣ አማራ ደን ኢንተርፕራይይዝ፣ ደሴ ማዕድን ውሃ፣ ኮንቦልቻ ዶሮ ሀብት ልማት ኢንተርፕራይዝ፣ ገራዶ ዶሮ እርባታ፣ ዴሴ ግብዓት ግንባታ ማመረቻ ይገኙበታል።

ሌሎች ስምንት ፋብሪካዎች መካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 24ቱ ደግሞ ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ስራ መመለስ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በዚህም ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞች ከስራ ገበታ ውጭ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የፈጸመው ጉዳት ትውልዱን በኢኮኖሚ በመጉዳት አገር የማፍረስ ዓላማ ያነገበ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የወደሙ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ስራ በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ  ከኮምቦልቻ ከተማ አሰተዳደርና ባለሃብቶች ጋር ውይይት ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ የጅምላ ሳይሆን በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ለሚሹ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ለመስጠት ይሰራል ነው ያሉት።

በዚህም ጉዳት የደረሰባቸውን ፋብሪካዎች ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን አሟልተው እንዲያገግሙ መንግስት በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ባለሙያዎችን  ወደ ስፍራው ለማሰማራት፣ የተቋረጡ የመሰረተ ልማት ተቋማት ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

የፊታችን ሰኞ በተመሳሳይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን እና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የጋራ ውይይት እንደሚኖር ተናግረዋል።

ጥናት ከተደረገባቸው የኮምቦልቻና ደሴ አካባቢዎች በተጨማሪ በአፋር ክልል ኢንዱስትሪዎች ላይም  በመተሳሳይ አጥኚ ቡደን መሰማራቱን ገልጸው፤ ውጤቱንም ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ወቅቱ የአምራች ኢንዱስትሪው የሚፈተንበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ለአገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ ሰጥቶ በመጠቀም ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት ሲመጡ የአገር ውስጥ ምርቶችን እንዲገዙና ከዚህ ባለፈ በኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ባለሃብቶች ውድመት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ በማልማት ረገድ ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በተለይ የጥቃቅን አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ይሕን አጋጣሚ በመጠቀም አስፈላጊ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማበረታታት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡