የማዕድን ሀብትን በአግባቡ ለማልማት በትኩረት ይሰራል – ሚኒስቴሩ

146

ጅማ፣ ታህሳስ 07/2014(ኢዜአ) የማእድን ሀብትን በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራ የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።

በማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቴዎስ የተመራ ልዑክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በማዕድን ዘርፋ በትብብር ለመስራት በሚቻልበት ዙሪያ በቦንጋ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው በወቅቱ እንደገለጹት በሀገሪቱ ለማዕድን ዘርፍ  እድገት ትኩረት ተሰጥታል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በማእድን ሀብቱ ከሚታወቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው በክልሉ የማእድን ሀብትን በአግባቡ በማልማት ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማዋል በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

“የማእድን ዘርፉን ለማጠናከር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለክልሉ ማዕድን ቢሮ የአንድ ተሽከርካሪ፣ የኮምፒውተርና ኤሌትሮኒክስ  ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል” ብለዋል።

በዘርፋ የሚታዩ ክፍተቶችን በትብብር ለመፍታት በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

የአመታት በክልል የመደራጀት ጥያቄ  ምላሽ አግኝቶ የክልሉ መንግስት በይፋ ተመስርቶ ለህዝቡ አገልገሎት መስጠት በመጀመሩም መደሰታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ተገቢና አስፈላጊ  መሆኑን ገልጸው በክልሉ ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ህብረተሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል” ብለዋል።

የማዕድን ዘርፍ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሰላምና የጸጥታ ሁኔታውን ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።