የሽብር ቡድኑ በደሴ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና መሳሪያዎችና መድኃኒት አውድሟል

63

ታህሳስ 7/2014/ኢዜአ/ አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና መሳሪያዎች፣ መድኃኒትና መገልገያ እቃዎችን ማውደሙን በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደሴ ቅርንጫፍ አስታወቀ።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከሚዘርፋቸውና ከሚያወድማቸው ተቋማት መካከል ቀዳሚዎቹ የሕክምና ተቋሟት ናቸው።

ከደብረሲና ጀምሮ ሸዋሮቢት፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ሐይቅ፣ ጋይንትና በአፋር ክልልም የሚገኙ የጤና ተቋማትን ዘርፏል አውድሟል።

የኤጀንሲው የደሴ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቴ ሹሜ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው በአማራ ክልል 58 እና በአፋር ሁለት ወረዳዎች የሚገኙ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሕዝብ የሚያገለግል ነበር።

በቀጠናው ያሉ 29 ሆስፒታሎች፣ ከ300 በላይ ጤና ጣቢያዎች፣ የመከላከያና የቀይ መስቀል ክሊኒኮች እና የግል የሕክምና ተቋማትንም እንዲሁ።

ይሁንና የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ዘረፋና ውድመት ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሕክምና መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶችና የመገልገያ እቃዎችን አጥቷል ብለዋል።

በዚህም የፖሊዮ፣ የኤች.አይ.ቪ፣ የኮቪድ-19 ክትባትና የካንሰር መድኃኒቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም