የአሸባሪውን የጥፋት እድሜ ለማሳጠር የህዝቡ ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

53

ደብረ ታቦር ታህሳስ 7/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪውንና ወራሪውን የህወሃት ቡድን የጥፋት እድሜ ለማሳጠር የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን ያልተቋረጠ ሁለተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አስታወቁ፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የምስራቅ ጎጃም ዞን የባሶ ሊበን ወረዳ ተወላጆች ከ500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ በጋሸና ግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል ድጋፍ አድርገዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የጋይንት-ጋሸና ግንባር ሎጅስቲክ አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ በድጋፍ ርክክቡ ላይ እንደገለጹት አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ከነክፉ ሃሳቡና ድርጊቱ በጋራ ማሰወገድ ከሁሉም የሚጠበቅ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

የሽብር ቡድኑ በገባባቸው አካባቢዎች በዚህ ዘመን የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታሰብ ዘግናኝ ግፍና በደል በህዝብ ላይ መፈጸሙን ጠቁመው "አሸባሪ ቡድኑ ምን ያህል የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባሩ አረጋግጧል" ብለዋል ።

"በሽብር ቡድኑ የጭካኔ ተግባር የተቆጣው የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ወራሪውን በየቦታው እየቀጣው ነው" ብለዋል፡፡

በየግንባሩ ለሚገኙ ድሎች የህብረተሰቡ ሁለተናዊ ድጋፍ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ጠቁመው የሽብር ቡድኑ ተጨማሪ ግፍና በደል እንዳይፈፅም እድሜውን ለማሳጠር የመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

"የደቡብ ጎንደር ህዝብ ታሪክ የማይረሳው አኩሪ ገድል እየፈጸመ ነው" ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው የተለያዩ ስንቆችን እስከ ግንባር ድረስ ለስራዊቱ በማድረስ  ደጀንነቱን እያረጋገጠ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በዞኑ 21 ወረዳዎች  የሚገኘው ህዝብ እስካሁን ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስንቅ ለሰራዊቱ ማድረሱን አመልክተዋል፡፡

ከዞኑ ህዝብ ለህልውና ዘመቻው በጥሬ ገንዘብም እስካሁን  ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን ጨምረው ገልጸዋል ።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የባሶ ሊበን ወረዳ ተወላጆችም ዛሬ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል አስተዳዳሪው ድጋፉ  ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚኖሩ የባሶ ሊበን ወረዳ ተወላጆችና የድጋፉ አስተባባሪ አቶ አማረ ጥበቡ በበኩላቸው "ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ መተጋገዝ፣ መረዳዳትና መተባበር የግድ ነው" ብለዋል፡፡

"የሽብር ቡድኑ እድሜ አጥሮ ሀገራችንንና ህዝባችንን ከስጋት ለመታደግ አስከ ህይወት መስዋትነት ለመከፍል ዝግጁ ነን" ሲሉም አክለዋል ፡፡

ህብረተሰቡን አስተባብረው ከ500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ብስኩት፣ ስኳርና በሶ፤ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ቁሳቁሶች ዛሬ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ ለአገርና ህዝብ  ሲሉ እየተፋለሙ ለሚገኙ መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች የተበረከተ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው  ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም