በኮምቦልቻ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ያረፈው የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት በትር

167

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 07/2014(ኢዜአ) በኮምቦልቻ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ያረፈው የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት በትር

ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ኮሪደሮች አንዷ በሆነችው የደቡብ ወሎዋ ኮምቦልቻ ከተማ ከ200 በላይ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደስራ ተሰማርተዋል፤ ከ8 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ስራ እድል ፈጥረዋል።

የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ኃይል በከተማዋ በቆየባቸው ቀናት በርካታ ኢንዱስትሪዎች ላይ መጠነ ሰፊ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል፡፡

እነዚህ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ የጎላ ሚና የነበራቸው ናቸው።

ከሰሞኑ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተመራ የጋዜጦች እና የጉዳቱን መጠን የሚያጠና የባለሙያዎች ቡድን የደረሰውን ውድመት ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

አሸባሪ ቡድኑ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማሰማራት ጭምር በእያንዳንዱ ፋብሪካ ላይ ቁልፍ የማሽን መሳሪያዎችን ነቃቅሏል፤ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ መለዋወጫዎችን ሙሉ በሙሉ ዘርፏል።

በሁሉም ፋብሪካዎችን አስተዳድር ቢሮ መገልገያዎችን እና በገንዘብ የማይተመኑ ውድ ሰነዶችን ሙሉ በሙሉ አውድሟቸዋል።

በአብዛኞቹ ፋብሪካዎች ረቂቅ መሳሪያዎች ሳይቀር በወራሪው ቡድኑ ተነቅለው መወሰዳቸውንና ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን የፋብሪካዎቹ የስራ ኃላፊዎች አስረድተዋል።

ከዚህ ከተጋለጡት መካከልም በሁዋክሱ ጨርቃ ጨርቅ፣ በአማር ከረጢት ፋብሪካ፣ በሒፋም/ሰይድ አሊ ከረጢት ፋብሪካ እና በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ አምራች ኩባንያዎች ይገኙበታል።

ሁዋክሱ የተሰኘው የቻይና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የሰው ሀብትና ጠቅላላ አገልግሎት ዋና ኃላፊ አቶ ንጉሴ ገብሬ እንደሚሉት፤ በ2006 ወደ ስራ የገባውና ለ240 ሰራተኞችን የቀጠረው ድርጅት በምርቶች፣ በግብዓት፣ በማሽኖችና ኮንቴነሮች ላይ በደረሰበት ዘረፋ ከ52 ሚሊዮን ብር ጉዳት ደርሶበታል።

ከ300 በላይ ሰራተኞች በሚያስተዳድረው በሒፋም/ሰይድ አሊ የማዳበሪያ ከረጢት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ሚፍታህ አራጌ በበኩላቸው ከ80 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የፋብሪካው የጥገና መሳሪያዎች፣ ኮንቲኔሮች፣ መለዋወጫዎች እና የማሽን ማንቀሳቀሻ ቁልፍ ኮምፒተራይዝድ ማሽኖች ተመርጠው ተዘርፈዋል ነው ያሉት፡፡

የሒፋም/ሰይድ አሊ የማዳበሪያ ከረጢት ፋብሪካ ባለቤት አቶ ሰይድ አሊ፤ አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰው ጥፋይ የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይጠበቅ እና የአማራ ህዝብ ላይ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ጫና መፍጠርን ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰባቸው ጥፋት ሳይበግራቸው በእልህና በቁጭት ወደ ስራ ለመመለስ እንደሚፈልጉ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የፌዴራል መንግስትና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ትብብር እንደሚሹ ጠቁመዋል፡፡

በአማር የከረጢት እና ፕላስቲክ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አያሌው እንዳሉት፤ 500 በላይ ሰራተኞችን በሚያስተዳድረው ድርጅታቸው ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁልፍ የማሽን አካል ክፍሎች፣ በምርቶች፣ በመለዋወጫዎች እና በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ ዘረፋ እና ውድመት ተዳርጓል።

ከ4 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ስራ እድል የፈጠረው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሸዶች እስከ ኩሽና ድረስ ከፍተኛ ዘረፋ ተፈጽሞበታል ያሉት ደግሞ ፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ሰይድ ናቸው፡፡

ፓርኩን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ከ300 በላይ ሰራተኞችን የያዘው “ኢትውድ ማኑፋክቸሪንግ” የተሰኘው የቻይና የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ ላይም ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ጨምሮ ግምቱ ያልታወቀ ዘረፋ ተፈጽሟል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በተመሳሳይ ሌሎች የክልሉ የልማት ድርጅቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የፋብሪካው የስራ ኃላፊዎች መንግስትን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊው ትብብር ከተደረገላቸው በአጠረ ጊዜ ውስጥ የወደሙ ንብረቶችን በመተካት ወደስራ ለመመለስ ቁርጠኛ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባይነህ አበባው አሸባሪ ቡድኑ ከኢንቨስትመንት አዋጁም ሆነ ከዓለም አቀፍ ህግ በተቃረነ መልኩ በኢንዱስትሪዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከባለሃብቶች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

በውይይታቸውም በተለይ ከግብዓት፣ የውጭ ምንዛሬና መብራትና ቴሌኮምን ጨምሮ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባለሃብቶች ያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።