መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለአርሶ አደሮች 225 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ

144

ጎባ ታህሳስ 7/2014(ኢዜአ) መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በኩታ ገጠም የግብርና አሰራር ዘዴ ስንዴን በበጋ መስኖ ለሚያለሙ የአጋርፋና ጋሰራ ወረዳ አርሶ አደሮች 225 ኩንታል ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ መንግስት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የጀመረውን ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ በምርጥ ዘር አቅርቦት ለመደገፍ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የአጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በዘር ድጋፉ በመታገዝና የውኃ አማራጮችን በመጠቀም ማሳቸውን በዘር መሸፈን መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምር ማህበረሰብ አቀፍና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ሌንጮ ሳሙኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው  ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ ምርምርን መሰረት ያደረጉ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በአጋርፋና ጋሰራ ወረዳዎች ውስጥ በኩታ ገጠም ለተደራጁ 225 አርሶ አደሮች ያደረገው የምርጥ ዘር ድጋፍ የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

ለአርሶ አደሮቹ የተደረገው 225 ኩንታል ምርጥ ዘር በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጥና ከምርምር ተቋማት የተለቀቀ “ኪንግ በርድ” የተሰኘ ዝርያ መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ ሌንጮ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ መንግስት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ  ለመተካት ስንዴን በመስኖ የማልማት ጥረትን በምርጥ ዘር አቅርቦት የሚደግፍ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለምርጥ ዘር ግዥ አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ማድረጉን ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲው ለአርሶ አደሮች እያደረገ ያለው ሙያዊ እገዛና ክትትል እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የአጋርፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወል ኢብራሂም በበኩላቸው መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የአካባቢውን አርሶ አደር ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በአካባቢው የሚገኘውን የውኃ አማራጭ ተጠቅሞ ስንዴን በመስኖ እንዲያለማ እያደረገ ያለው ድጋፍ አርአያነት ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የምርጥ ዘር ድጋፍ ከተደረገላቸው የአጋርፋ ወረዳ የሀምቤንቱ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር አማን ፈቶ ” የህልውና ዘመቻን ከመደገፍ በተጓዳኝ ከዩኒቨርሲቲው ያገኙትን ምርጥ ዘር በመጠቀም ስንዴን በኩታ ገጠም እያለማን ነው፤ ለዚህም ተቋሙን እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡

በግብርና ስራ የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም ከሚጠቀሙት የአካባቢ ዝሪያ የልፋታቸውን ያህል ምርት ሳያገኙ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር አማን አብዳ ናቸው፡፡

“ዩኒቨርሲቲው በሰጠን ምርጥ የስንዴ ዝሪያ ምርታችንን  ለማሳደግ እንተጋለን ” ብለዋል።  

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ በስንዴ ሰብል ላይ የሚደረገው ምርምር ቀጣይነት እንዲኖረው የስንዴ ምርምር የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም ግብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

በባሌ ዞን በ2013/2014 የምርት ወቅት ከ19ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ በሁለት ዙር ለማልማት የታቀደ ሲሆን እስከ አሁን በተደረገ እንቅስቃሴ 5 ሺህ ሄክታሩ ታርሶ በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡