በዞኑ ለዘማች ቤተሰቦች ከ485 ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ የመኽር ሰብል ተሰበሰበ

129

አምቦ ታህሳስ 7/2014 (ኢዜአ) በምእራብ ሸዋ ዞን ግንባር ለዘመቱ የሚሊሻ ቤተሰቦች ከ485 ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ የመኽር ሰብል መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ከ33 የዞን ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የመንግስት ሰራተኞች በአምቦ ወረዳ አማሮ የገጠር ቀበሌ የዘማች ቤተሰቦችን የደረሰ ሰብል ዛሬ በዘመቻ ሰብስበዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ኡማ ለኢዜአ እንደገለጹት የአሸባሪውን ህወሃት ወረራ ለመቀልበስ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ለዘመቱ ቤተሰቦች የሰብል ስብሰባ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች  ይዞታ ከሆነ ከ485 ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ የመኽር ሰብል በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

“የዞን ሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞችም ዛሬ ያካሄዱት የሰብል ስብሰባ የዚሁ አካል ነው ” ብለዋል ።

በህብረተሰብ ተሳትፎ ለዘማች ቤተሰቦች የተደረገው የሰብል ስብሰባ በገንዘብ ሲተመን 820 ሺህ 950 ብር ግምት ያለው መሆኑን ተናግረዋል ።

ለዘማች ቤተሰቦች እየተደረገ ያለው ድጋፍና እንክብካቤ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።

በሰብል ስብሰባው ከተሳተፉ የመንግስት ሰራተኞች መካከል የዞኑ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሰራተኛ ወይዘሮ አዲሰ ሻንቆ “ለሃገራቸው አንድነት ሲሉ ህይወታቸውን ለመገበር ወደ ግንባር ለሄዱ የሚሊሻ አባላት ቤተሰባቸውን መንከባከብ የሁላችንም ኃላፊነት ነው” ብለዋል።

“ሰላም ለማስከበር ለዘመቱ የሚሊሻ ቤተሰቦችን መደገፍ በያሉበት ዘማች የሚያስብል ነው” ሲሉም አክለዋል።  

የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባልደረባ አቶ ወርቅነህ ሁንዴሳ በበኩላቸው አሸባሪዎቹ ህውሃትና ሸኔን ለመፋለም  ወደ ግንባር  ለዘመቱ  የሚሊሻ አባላት  ሰብል ለመሰብሰብ ሌሎችን አስተባብረው ወደ ስራው መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ሀገራችን ከአሸባሪዎቹ ሙሉ በሙሉ ነጻ እስከምትሆን ድረስ ለዘማች ቤተሰቦች ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈልም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በምእራብ ሸዋ ዞን በ2013/14 ምርት ዘመን መኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 607 ሺህ 109 ሄክታር መሬት 468 ሺህ 157 ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡