በኦሮሚያ ክልል በ162 ሚሊዮን ብር የእንስሳት መኖ ልማት እየተከናወነ ነው

121

ታህሳስ 7/2014/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል በ162 ሚሊዮን ብር የእንስሳት መኖ ልማት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የእንስሳት ልማት ዘርፍ ኃላፊ ቶሌራ ደበላ፤ በክልሉ አምስት ዞኖች የተከሰተው ድርቅ በተለይም በእንስሳት ላይ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በቦረና ዞኖች፣ በምስራቅ ባሌና ሁለቱ ጉጂዎችና በምዕራብ ሀረርጌ ቆላማ አካባቢ የተወሰኑ ወረዳዎች ድርቅ መከሰቱን ገልጸዋል።

በቦረና ዞን 11 ወረዳዎች፣ በምስራቅ ባሌ 5 ወረዳዎች፣ በምዕራብ ሀረርጌ 5 ወረዳዎች፣ በጉጂ 4 ወረዳዎች ድርቁ መከሰቱን ሃላፊው ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በእንሰሳቱ ላይ ድርቁ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል በአንድ ወር ሊደረስ የሚችል 900 ኩንታል የእንስሳት መኖ ተዘርቶ በመስኖ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

በምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ አካባቢ የመስኖ ልማቱ እየተከናወነ ሲሆን በባሌ አካባቢም በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።

ለእንስሳቱ መኖ ማከማቻ ባንክ የሚሆኑ ትላልቅ መጋዘኖች ግንባታም ይካሄዳል ነው ያሉት።

አሰራሩ በእንሰሳት ሃብት ልማት ላይ የሚደርሰውን ችግር በዘላቂነት ለመከላከል የሚረዳ መሆኑንም አቶ ቶሌራ አብራርተዋል።

በቦረና አከባቢ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን የእንሰሳት ሃብት መኖሩን የጠቀሱት ሃላፊው በአካባቢው ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ በተወሰኑት ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ለእንስሳቱ የውሃ እና የሳር አቅርቦት መኖሩን ጠቅሰው በመንግስት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በህብረተሰቡ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች እንስሳቶቻቸውን በጊዜያዊነት ድርቅ ወደ ሌለበት አካባቢ እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።