“እናት አገር ስትጣራ አቤት የማይል ኢትዮጵያዊ የለም”

127

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 07/2014(ኢዜአ) “እናት አገር ስትጣራ አቤት የማይል ኢትዮጵያዊ የለም” ይላሉ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በዝግጅት ላይ የሚገኙ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በመላው ዓለም የሚገኙ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች እስከ ታህሳስ 29 ቀን 2014 ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

ኢዜአ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ አስመልክቶ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትን አነጋግሯል።

የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪው አቶ ደሳለኝ አበራ ጥሪው የእናት አገር ኢትዮጵያን “በችግሬ ጊዜ ድረሱልኝ” የሚል ትልቅ አደራና ኃላፊነትን ያዘለ ነው ይላሉ።

እናት አገር ስትጣራ “አቤት” የማይል ኢትዮጵያዊ ባለመኖሩም ዳያስፖራው በከፍተኛ ሁኔታ ተነሳስቶ ወደ አገር ቤት ለመግባት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚመጣው የኢትዮጵያን ችግር ለመካፈልና ለመርዳት መሆኑንም አክለዋል።

ኢትዮጵያ እየደረሰባት ያለውን የኢኮኖሚ ጫና እንድትቋቋም ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ሲመጣ ገንዘቡን ፈሰስ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ነው አቶ ደሳለኝ የተናገሩት።

ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ይዞት የሚመጣውን የውጭ ምንዛሬ በሕጋዊ መንገድ በመቀየር ኢትዮጵያን እንዲያግዝ ቅስቀሳ እየተደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ወደ አገር ቤት ሲመጡ ለተፈናቀሉ ወገኖችን እና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እንደሚያደርጉም እምነታቸውን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ የዳያስፖራው መምጣት የቱሪዝም ዘርፉንና ኢኮኖሚውን የማነቃቃት ዕድሉ ሰፊ ነው።

በእንግሊዝ ማንችስተር ከተማ የሚኖሩት አቶ አበበ ቶላ በበኩላቸው ጥሪው የውጭ አገራት በኢትዮጵያ ‘ሠላም የለም’ በሚል ዜጎቻቸውን እያስወጡ ባሉበት ወቅት መሆኑ ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ቆም ብለው እንዲመለከቱ ያደርጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሁል ጊዜም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጎን መሆኑንና ይህንንም ወደ አገር ቤት በመምጣት በተግባር ያሳያል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት መስኮች ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከቪዛ ጀምሮ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ አሰራሮች አስፈላጊው ማሻሻያ ተድርጎባቸው ቀልጣፋና ፈጣን ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ዳያስፖራዎችም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አገር ያቀረበችውን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት በመትመም አለኝታነታቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸው ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አገራቸው መምጣት ያልቻሉትም ለኢትዮጵያ ሊያደርጉ የሚችሉትን ድጋፍ ባሉበት ሆነው ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ዳያስፖራው በቀረበው ጥሪ ወደ አገር ቤት በመምጣት የዚህ ታሪክ አካል መሆን አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት እንዲመጡ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ እስካሁን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለመምጣት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የጥሪው ዓላማ የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት፣ በውጭ መገናኛ ብዙኃን ስለ ኢትዮጵያ የሚሰራጨውን ሐሰተኛ መረጃ በመቀልበስ እውነቱን ለዓለም ማሳወቅ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችና የልማት ቦታዎች ማስተዋወቅ እንደሆነም መገለጹ ይታወቃል።