የሽብር ቡድኑ በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ የሕዳሴ ግድብና የሌሎች ፕሮጀክቶችን ከ100 በላይ ኮንቴይነር እቃዎች አውድሟል

93

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 07/ 2014 (ኢዜአ) የሽብር ቡድኑ ህወሓት በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ለሕዳሴ ግድብና የሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ከ100 በላይ ኮንቴይነር እቃዎች ላይ ዘረፋና ውድመት ማድረሱን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።

አሸባሪው ሕወሓት ስልጣን ላይ በነበረበትም ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በታቀደለት መልኩ እንዳይሄድ በርካታ ችግሮችን ሲፈጥር ቆይቷል።

በ'ሜቴክ' አማካኝነት ግንባታው እንዲጓተት በማድረግ፣ ተጨማሪ የግንባታ ወጪና ጊዜ እንዲጨምርም አድርጓል።

ከዚህም አልፎ ኩባንያው ግንባታውን ያከናወነበት የግንባታ እቃዎች ጥራት ጭምር አጠራጣሪ ሆነው በመገኘታቸው ግንባታው ፈርሶ በድጋሚ እንዲሰራም ሆኗል።

የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ የሽብር ቡድኑ ህወሓት አሁንም በሁለት ደረቅ ወደቦች ላይ ያደረሰው ውድመት ከባድ መሆኑን ተናግረዋል።

ውድመትና ዘረፋ ከደረሰባቸው ደረቅ ወደብና ተርሚናል መካከል በዓመት 14 ሺህ ኮንቴይነር የሚያስተናግደው የመቀሌ ደረቅ ወደብ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓመት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያስገኝ በነበረው በዚህ ወደብ የባለሃብቶችን እቃዎች የያዙ 209 ኮንቴይነሮች ለዘረፋና ውድመት ተዳርገዋል።

የአንዱ ዋጋ እስከ 20 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ትላልቅ ማሽነሪዎች መውደማቸውን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የሽብር ቡድኑ በወረራ ወደ አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ሲገባ የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ላይ ተመሳሳይ ጥፋት መፈጸሙን ገልጸዋል።

በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ተከማችተው ከነበሩ 251 ኮንቴይነሮች ከ100 በላይ የሚሆኑት የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን እቃዎች የያዙ እንደነበሩ ጠቁመዋል አቶ ሮባ።

ለዘረፋ የታጋለጡት የልማት ፕሮጀክቶች ንብረቶች ለሌላ ጥቅም እንደማይውሉ እየታወቀ የሽብር ቡድኑ ሆን ብሎ ለውድመት ዳርጓቸዋል ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ በኮንቴይነሮች ውስጥ የነበሩትን ብቻ ሳይሆን በግምሩክ መጋዘኖች የተከማቹ እቃዎች፣ ማሽነሪዎችና ቢሮዎችንም ማውደሙን ተናግረዋል።

የደረሰው ጉዳት በዝርዝር ባይታወቅም ውድመቱ ከፍተኛ መሆኑንም አክለዋል።

ኮንቴይነሮቹ የያዟቸው እቃዎች ሳይካተቱ በሁለቱ ደረቅ ወደቦች የነበሩት የባዶ ኮንቴይነሮች ዋጋ ብቻ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመትም ገልጸዋል።

ለውድመት የተዳረጉት በውጭ ምንዛሬ የተገዙ ለኮንቴይነሮች መጫኛና ማውረጃ የሚያገለግሉ ትላልቅ ማሽነሪዎች ግምታዊ ዋጋም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ሮባ ገለጻ በተለይ በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ኮንቴይነሮች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ቢሞከርም የሽብር ቡድኑ ማሽኖችና ሙያተኞችን ከሌላ ቦታ በማምጣት ዘረፋ ፈጽሟል።

ድርጅቱ በቀጣይ የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር አጥንቶ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም