በደብረ ማርቆስ ተማሪዎች የ''በቃ'' ዘመቻን በመቀላቀል ሰልፍ አካሄዱ

115

ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2014 ---የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የምዕራባዊያንን ጫና በመቃወም የ''በቃ'' ዘመቻን በመቀላቀል ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይሁኔ መለሰ በእዚህ ወቅት እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በንጹሀን ላይ ለማየትና ለመስማት የሚከብድ አሳዛኝ የጭካኔ ድርጊት ፈፅሟል።

የጥፋት ቡድኑ አገር የሚገነባ የተማረ ትውልድ እንዳይኖር በማሰብ የመማሪያ ግብአቶችን ከመዝረፍ ባለፈ የትምህርት ተቋማትን በማውደም እኩይ ተግባሩን አሳይቷል።

ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች የነበሩ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ በመሆናቸው በእጅጉ ማዘናቸውን ተናግረዋል

ተማሪዎች በየትምህርት ቤቱ የአቅማቸውን በማዋጣት ከ500 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ለፀጥታ ሃይሉ በመለገስ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራትና አሜሪካ አሸባሪውን ህወሓት በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ጫናና የመገናኛ ብዙሀኖቻቸውን ሀሰተኛ ዘገባ ለመቃወም የ''በቃ''ን ዘመቻ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

"ታዳጊ ተማሪዎቹ በአደባባይ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ከፖለቲካም ሆነ ከኢኮኖሚ ተፅዕኖ ነፃ የሆነች አገር እንድትኖራቸው የፀና ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል" ብለዋል።

ከሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል የደብዛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ደሳለኝ ጫኔ በበኩሉ የህወሓት የሽብር ቡድን የትምህርት ተቋማትን በማውደም የማይረሳ ጠባሳ እንደጣለባቸው ተናግሯል።

"በተለይ የተማረ የሰው ሃይል እንዳይኖር ለማድረግ በትምህርት ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት ሁሌም አይረሳም" ብሏል።

አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት አሸባሪውን ህወሓት በግልጽ ከማውገዝ ፈንታ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረጉ ስለሆነ በቃችሁ የሚለውን ድምጹን ለማሰማት ሰልፍ መውጣቱን ተናግሯል

ቀደም ሲልም ለህልውና ዘመቻው 150 ብር ከማዋጣቱም በተጨማሪ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ለአንድ ሳምንት በመሰብሰብ የበኩሉን አስተዋጾ ማድረጉን አስታውቋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የተክለሃይማኖት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ትዕግስት አበበ በበኩሏ "በአገራችን ላይ እየተስተዋለ ያለው የውጭ ጣልቃ ገብነት ሊቆም ይገባል" ብላለች።

የሽብር ቡድን አካላቸው ገና ባልጠነከረ ሴት እህቶቻችን ላይ እየፈፀመ ያለው ግፍና መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን እንዲሁም የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም አደባባይ መውጣቷን ተናግራለች፤

አንዳንድ የምዕራባዊያን ሃገራት አሸባሪውን ሀወሓት ከመደገፍ ተቆጥበው ድርጊቱን ''በቃ'' ብለው ሊያስቆሙ እንደሚገባ ገልጻለች።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ  "ኢትዮጵያን እንደሊቢያ እና ሶሪያ ለማድረግ የምትፈልጉ አገራት እጃችሁን አንሱ ፤ሀሳባችሁን ቀይሩ! ፤አሸባሪው ህወሓት በትምህርት ተቋማት ላይ ኪሳራ አድርሷል! ፤ አሜሪካ እና አውሮፓዊያን በኢትዮጵያ ላይ የምታደርጉትን ጫና እንድታቆሙ እኛ ተማሪዎች እንጠይቃለን የሚሉ መፈክሮች በተማሪዎቹ ተስተጋብተዋል።

እንዲሁም ''በቃ!''፣ ጀግኖቻችን እኛ እስክንደርስ ኢትዮጵያን አደራ!፣ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ኩራት እንጂ የምዕራባዊያን ማላገጫ አለመሆኗ  ታሪክ ምስክራችን ነው!  የሚሉና መሰል መፈክሮችም በተማሪዎቹ የተስተጋቡ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም