የተባበሩት መንግስታትድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የጠራው ስብሰባ ኢ-ፍትሃዊ ነው

237

ሶዶ ታህሳስ 7/2014 (ኢዜአ ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አፋጣኝ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እያሉ ኢትዮጵያን በተመለከተ የጠራው ስብሰባ ኢ-ፍትሐዊ መሆኑ ተመለከተ።

የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤቱ  የጠራው ስብሰባን አስመልክቶ  በወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪና የህግ ባለሙያ አቶ መብራቱ በለጠ ለኢዜአ እንደገለፁት በርካታ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እያሉ በኢትዮጵያ ጉዳይ ምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ መጥራቱ  ኢ-ፍትሐዊነቱን በግልጽ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በአሸባሪው ህወሀት እየተፈፀሙ የሚገኙ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቢኖሩም እንዳላየ በቸልተኝነት ማለፉን ጠቁመዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት ተገቢውን ህጋዊ አሰራር በመከተል ሀገር የማረጋጋት ስራ እየሰራች ባለችበት ወቅት ስብሰባ መጠራቱ ተገቢነት የሌለው መሆኑን አመልክተዋል።

አሸባሪው ህወሃት ያደረሰው ጭፍጨፋና ውደመት እየታወቀ በዝምታ አልፎ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የጠራው ስብሰባ ምክር ቤቱ ለሽብር ቡድኑ ያለውን ወገንተኛነት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ካሁን ቀደም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ጥናት መደረጉን ያስታወሱት የሶዶ ዩኒቨርሲቲ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ጳውሎስ ወርቁ ናቸው።

ጥናቱ ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ አለመደረጉን አረጋግጦ እንደነበረም ጠቁመዋል።

“ስብሰባው መጠራቱ በራሱ ወቅቱን የጠበቀ ባለመሆኑ አድሏዊነቱንም ጎልቶ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“አክለውም ምክር ቤቱ የሽብር ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ያደረሰውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችና እልቂት እንዳላየ ከማለፉ ባሻገር በሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ስብሰባ መጥራቱ በየትኛውም ሚዛን ገለልተኛ ሊያደርገው አይችልም” ነው ያሉት።

በሀገሪቱ አንገብጋቢና ትኩረት የሚፈልጉ በርካታ ጉዳዮች ባሉበት ሁኔታ ልዩ ስብሰባ መጠራቱ ተገቢነት እንደሌለው አስታውቀዋል።