አሸባሪው የህወሃት ቡድንን የሚያወግዝ ክልል አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ነገ በባህርዳር ይካሄዳል

152

ባህር ዳር ታህሳስ 7/2014 (ኢዜአ) አሸባሪውና ወራሪው የህወሃት ቡድን ህጻናትና ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር እየፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያወግዝ ክልል አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ነገ በባህር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ክልሉን መውረር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በህፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ላይ የአስገድዶ መድፈርና ሰብዓዊ ጥሰት እያደረሰ ቀጥሎበታል።

ቡድኑ እያደረሰ ባለው ጭፍጨፋም በርካታ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ወላጆቻቸውን በማጣታቸው ያላሳዳጊ፣ አረጋዊያን ያለጧሪ እንዲቀሩ ማድረጉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ አቅዶ የተነሳው አሸባሪው ቡድን በክልሉ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ዘረፋና ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል።

ቡድኑ ከህፃናት ጀምሮ እስከ አዛውንት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር ለከፋ ስነ-ልቦና ችግር እየዳረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ከአሸባሪ ቡድኑ በተለቀቁ አካባቢዎች እስካሁን ለቢሮው የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት 147 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር መፈፀሙን ጠቅሰው፤ ከነዚህም ውስጥም 17ቱ ህፃናት መሆናቸውን አመላክተዋል።

በንፁሃን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ነገ  ከጥዋቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ 4 ሰዓት በባህር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ዓለም አቀፍ ህግን ያወጡ ሀገራት በተለይም አንዳንድ ምዕራባዊያን አሸባሪ ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ጥሰት እያዩ እንዳላዩ እያለፉ በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጡ ግንዛቤ ለመፍጠር  ነው።

ከዚህ ባለፈም አሸባሪ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ህግ ተጠያቂ እንዲሆንና አንዳንድ ሀገራትም የሚያደርጉትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ድምጽ ለማሰማት ጭምር እንደሆነ አብራርተዋል።

በሰልፉ ላይም ሁሉም የሴት አደረጃጀቶችና ሌላው ማህበረሰብም በመታደም አሸባሪው ቡድን እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል እንዲያወግዝም ወይዘሮ አስናቁ ጥሪ አቅርበዋል።

''አሸባሪው ቡድን እያደረሰ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር የዓለም ህብረተሰብ በአግባቡ እንዲረዳው በጋራ ልንነሳ ይገባል' ያሉት ደግሞ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ የሻረግ ፈንታሁን ናቸው።

አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልሞ የተነሳ በመሆኑ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እውነታውን ማስረዳት የእኛ ኃላፊነት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በሰልፉ ላይ ሁሉም ህብረተሰብ በመገኘት ቡድኑ በእናቶችና ህፃናት ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍና በደል ሊያወግዝ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም