አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ከልማት ውጭ አድርጓል

218

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአማራና የአፋር ክልሎች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ከልማት ውጭ ማድረጉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መለስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮ መኸር 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 375 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

ይሁንና የሽብር ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩት የአማራና የአፋር ክልሎች ለመኸር እርሻ የተዘጋጀውን መሬትና ሰብል አውድሟል፣ ዘርፏል፣ አቃጥሏል።

በክልሎቹ ከሚገኝ ለመኸር እርሻ የሚውል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በሚልቅ በዘር የተሸፈነ መሬት፣ ለምርት የደረሰ እና በማደግ ላይ የነበረን ሰብል ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ አድርጓል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ የአርሶ አደሩን መሬት በታንክና በመኪና ሄዶባቸዋል፣ የእርሻ መሬቱን የጅምላ መቃብር አድርጎታል ገሚሱንም ምሽግ ሰርቶበታል ብለዋል።

ወራሪው የአርሶ አደሩን የእርሻ መሳሪያዎች ዘርፎታል፣ ለእርሻ የሚጠቀምባቸውን በሬዎቹን አርዶ በልቶበታል፣ ነድቶ ወስዶበታል እንዲሁም ገድሎበታል ሲሉ ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም በአካባቢዎቹ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተረጋግተው እንዳያርሱ፣ ምርታቸውን እንዳይንከባከቡና በስጋት እንዲቆዩ ማድረጉንም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተር መለስ ገለጻ ይህንን የእርሻ ስራ ለማካካስ የአስቸኳይ ጊዜ ጥናት በማካሄድ የተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉና አካባቢዎቹ እንዲያገግሙ የማድረግ ስራ ተጀምሯል።

የአካባቢዎቹ ነዋሪዎችና አስተዳደሮች በቁጭት በመነሳት አርሶ አደሩ በመስኖ ስራ እርሻውን መከወን እንዲችል ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ለዘር የሚሆን ሰብል ሳይቀር መዝረፉን የገለጹት ዶክተር መለስ አርሶ አደሩ ለዘር የሚሆን ሰብል ከተለያዩ ሁኔታዎች እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አብዛኛው የአፋር ክልልና ከወረራ ነጻ የወጡ የአማራ ክልል አካባቢዎች ወደ ግብርና ስራቸው እየገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በግብርናው ዘርፍ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ጉዳቱን ለማካካስ የመስኖ ልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሆነም አክለዋል።

በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ እና የስንዴ መስኖ ልማት ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ እርሻ 310 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን፤ በተመሳሳይ በስንዴ 400 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከ154 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በሽብር ቡድኑ ወረራ የደረሰውን የመኸር እርሻ ጉዳት ለማካካስ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

-አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።