ለአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ በቀረበው ጥሪ እስካሁን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወደ አገር ቤት ለመምጣት ተዘጋጅተዋል

233

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 06/2014(ኢዜአ) አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት እንዲመጡ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ እስካሁን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ዝግጅታቸውን ማጠናቃቃቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት እንዲመጡ እየተደረገ ስላለው ዝግጅት መግለጫ ሰጥቷል።

የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንዲመጡ አገራዊ ጥሪ ተላልፏል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ እንድሪስ ወደ አገር ቤት የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበልና በቆይታቸውም ለአገራቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዕድል የሚፈጥሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህን ተግባራት በቅንጅት መምራት እንዲቻልም ኤጀንሲው የሚያስተባብረውና ቱሪዝም ሚኒስቴር በምክትል ሰብሳቢነት የሚሳተፍበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

ኮሚቴው አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ የሚመጡ እንግዶች ተሳትፎ የሚያደርጉባቸው የተለያዩ ሁነቶችን ማዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ይህ ጥሪ በኢትዮጵያ የደህንነት፣ የጉዞ፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና ተያያዥ ጉዳዮች ስጋት እንዳለ የሐሰት መረጃ ለሚነዙ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ይህን በመገንዘብ ወደ አገራቸው ለመምጣት ያሳዩት ቁርጠኝነት ሲነዛ የነበረውን ፕሮፖጋንዳ የቀለበሰም ጭምር ነው ብለዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ የአገሪቷን እውነታ ለማሳወቅ ያደረጉትን ትግል ወደ አገር ቤት በመግባት ለማስመስከር የሚመጡበትን ቀን በጉጉት እየጠበቁ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ጥሪው በተላለፈ ማግስት ተጓዦች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ መጀመራቸውን ጠቁመው እስካሁን ባለው ሂደትም ከታሰበው ቁጥር ከግማሽ በላይ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ዕድል ለመፍጠር የጊዜ ሰሌዳ መርሃ ግብሮች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በራሳቸው ተነሳሽነት አዳዲስ ሃሳቦችን በማመንጨት አበርክቷቸውን የሚያሰፉባቸው ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠርላቸውም ጥያቄ አቅርበዋል።

በዚህም ስራው በተቀናጀ መልኩ እንዲካሄድና የእነሱንም ፍላጎት ለማሟላት በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ መሆኑን ዶክተር መሀመድ ተናግረዋል።