ኮሌጆቹ ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቃይ ዜጎች አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አደረጉ

72

ሐረር ፤ ታህሳስ 6 ቀን 2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የሚገኙ የግል ኮሌጆች ለመከላከያ ሠራዊቱና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ዜጎች አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የጥሬ ገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረጉ።

ከድጋፉ ውስጥ ከ445ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ለመከላከያ ሠራዊት የተደረገ መሆኑን ዛሬ በተካሄደው የርክክብ ሥነ -ሥርዓት ላይ ተገልጿል።

እንዲሁም በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ምግብ ነክ፣አልባሳትና የቤት መገልገያ ቁሳቁስ ለግሰዋል።

የሐረሪ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናዎች አጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘከሪያ አብዱላዚዝ ኮሌጆቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉን አሰባስበው  ለሠራዊቱና ለተፈናቃይ ወገኖች እንዲደርስ የሚያደርጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የአፈረንቀሎ፣የሉሲና የሆርን ኮሌጆች ተወካዮች ኮሌጁ የሀገር ሰላምና ደህንነት እስኪረጋገጥና ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በክልሉ የሚገኙት ኮሌጆች ቀደም ሲልም ለመከላከያ  ሠራዊት  ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም