ፌዴሬሽኑ በአፋር ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ ድጋፍ አደረገ

172

ሰመራ፤ ታህሳስ 6/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል ወረራ በፈጸመበት ወቅት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ።

የድጋፍ ርክክቡ ዛሬ በተካሄደበት ወቅት የፌዴሬሽኑ  የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ፎዝያ ኢድሪስ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት በአፋር እና አማራ ክልሎች በዜጎች ላይ ያደረሰው ሰቆቃና ያስከተለው የንብረት ውድመት በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።

ፌዴሬሽኑ ከመንግስትና ከተጎጂ ወገኖች ጎን በመቆም የሚጠበቅበት ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

ፌደሬሽኑ ከአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እስከ መልሶ ማቋቋም በሚደረገው ጥረት የድርሻውን በመወጣት ከክልሉና ከተጎጂ ወገኖች ጎን እንደሚቆም ነው ወይዘሮ ፎዝያ ያስታወቁት።


“አትሌቲክስም ሆነ ሌላው የስፖርት ዓይነት የሚኖረው ሀገርና ህዝብ ሲኖሩ ነው” ያሉት ደግሞ የአፋር ክልል አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኡመር ኢብራሒም ናቸው።

አሸባሪው ህወሓት በሀገርና በዜጎች ላይ የደቀነው አደጋ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።


አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ዛሬ ያደረገው የምግብ ድጋፍ ለሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ተምሳሌት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፌደሬሽኑን ድጋፍ የተረከቡት የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን፤ ፌዴሬሽኑ ያደረገው  አስተዋጽኦ መንግስት ለተጎጂዎች የሚያደርገውን ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያግዝ በመግለጽ  ምስጋና አቅርበዋል።

በአሸባሪው  ወረራ ምክንያት በክልሉ  ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለምግብ እጥረት ችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪ የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው  ወረዳዎች ይኖሩ የነበሩ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም ጠቅሰዋል።

ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን  የእለት ደራሽ እርዳታ ማድረስ በመንግስትና በተወሰኑ አካላት ጥረት ብቻ ስለማይቻል አቅም ያላቸው ሁሉ  ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።