ባለፉት አምስት ወራት ከቆዳ ኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ 19 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

66

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 06/2014(ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ ያለፉት አምስት ወራት ከቆዳ ኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ 19 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የበጀት ዓመቱን አምስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እና በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግሮች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሽፈራው እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ከዘርፉ 26 ሚሊዮን 815 ሺህ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

በዚሁ መሰረት 19 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ወይንም የዕቅዱን 70 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአጎዋ የንግድ ሥርዓት መውጣቷን ተከትሎ ሊያጋጥማት የሚችለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት መተካት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገሪቷ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተደራሽ የሚሆኑባቸውን አማራጭ አገራት ማስፋት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

ይህም በተለይ በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ አገራት ገበያ ውስጥ ለመሳተፍና ተደራሽነትን ለማስፋት ከሚመለከታቸው አካላትና ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ለአብነትም በደቡብ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ክልሎች የበሬ ቆዳ በኮንትሮባንድ እየወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

በምስራቅ ኦሮሚያና በምስራቅ ሶማሌ እንዲሁም በምዕራብ ኦሮሚያ ጉጂና ቦረና አካባቢዎችም በተመሳሳይ  በኮንትሮባንድ እንዲወጣ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህ ሳቢያ በፋብሪካዎች ላይ እጥረት እያጋጠመና አገሪቷም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያጣች መሆኑን ገልጸዋል።

አገሪቷ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ እንዲህ አይነት ህገ-ወጥ ተግባር ላይ መሳተፍ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመረዳት የድርጊቱ ፈጻሚዎች እንዲታረሙም አሳስበዋል።

ሕገ-ወጦችን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድና ወደ ሕግ የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናልም ብለዋል።

በ2014 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከቆዳ ኢንደስትሪው 90 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ስለመሆኑ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም