የኔዘርላንድስ መንግስት በሕዝብ ከተመረጠው የኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

240

ታህሳስ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኔዘርላንድስ መንግስት በሕዝብ ከተመረጠው የኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንዲቆም በአገሪቱ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጠየቁ።

የ’በቃ’ ወይም #NoMore ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ የኔዘርላንድስ የዲፕሎማሲ ማዕከል ተብላ በምትጠራው ‘ዴን ሃግ’ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

ሰልፉ መነሻውን ‘ማሊቬልድ’ ከሚባል አካባቢ በመነሳት ወደ ኔዘርላንድስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመቀጠል ወደ አገሪቱ ፓርላማ በማቅናት መካሄዱን ኢዜአ ከሰልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሰልፉ ላይ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን፣ የሌሎች አፍሪካ አገሮች ዜጎችና ተወላጆች፣ ጃማይካውያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል።

ሰልፈኞቹ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ በሕዝብ ላይ እየፈጸሙት ያለውን ግፍና ሰቆቃ እንዲያወግዙና የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በኢትዮጵያ ላይ እያሰራጩ ያለውን ሀሰተኛ ዘገባ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በኔዘርላንድስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የኔዘርላንድ መንግስት በሕዝብ ከተመረጠው የኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ማሳሰባቸውም ተገልጿል።

ሰላማዊ ሰልፉን ያዘጋጁት በኔዘርላንድስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት ናቸው።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።