ወጣቱ የአባቶቹን ታሪክ ለመድገም እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው

65

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 06/2014(ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ እንደ ቀደምት አባቶቹ ሁሉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነቷን ለማስጠበቅ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን የኮርያ ዘማቾች ገለጹ።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ1950 እስከ 1953 በተካሄደው የኮሪያ ጦርነት ኢትዮጵያ የሰሜን ኮሪያን ወረራ ለመከላከል በመንግሥታቱ ድርጅት ጥላ ሥር ጦሯን አዝምታለች።

በወቅቱ የተመድን ጥሪ ተከትለው ወደ ኮሪያ ካቀኑት 16 አገራት መካከል ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ባካሄዷቸው የሽምቅና የደፈጣ ውጊያዎች ከፍተኛ ድል ማስመዝገብ ችለዋል።  

ያም ብቻ ሳይሆን ወደ ኮሪያ ካቀኑት 6 ሺህ 37 ወታደሮች 122 ብቻ ሲሰዉ፤ አንድም ወታደር በጦርነቱ አለመማረኩንና ኢትዮጵያ ትልቅ ጀብድ መፈጸሟን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።    

የዚያን ጊዜዎቹ የኮሪያ ዘማቾች ኢትዮጵያ ከጥንትም ለሠላም ዘብ የቆሙ ሕዝቦች አገር መሆኗን ጠቅሰው አሁንም ወጣቱ በሚፈጽማቸው ጀብዱዎች አኩሪ ታሪክ እያስመዘገበ ነው ይላሉ።

የአሁኑ ትውልድ አገሪቷ ላይ የተቃጣውን የሕልውና አደጋ በመቀልበስ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የሠላም ዘብነት እና የጀግንነት ታሪክ እየደገመ መሆኑንም መስክረዋል።

የኮሪያ ዘማቹ ሻለቃ አስፋው ተክለማርያም ወጣቱ ትውልድ በአንድነት በመቆም የአገሪቷን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ የሚያደርገው ርብርብ የሚበረታታ እንደሆነም ተናግረዋል።

ወጣቶች የአባቶችን ታሪክ እየደገሙ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ጠላት ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ በአፍሪካ ግንባር ቀደምት የሆነችን አገር ለማፈራረስ ቆርጦ ቢነሳም "የገጠመው ያልጠበቀው ነው" ያሉት ደግሞ የኮሪያ ዘማች አስር አለቃ ግርማ ሞላ ናቸው።

የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን አደራ ተቀብሎ አገሪቷን ከነሙሉ ክብሯ አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ቁርጠኝነት የሚበረታታ እና የሚወደስ ብለውታል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን እኔ ካልመራኋት አገር ትፈርሳለች በሚል እሳቤ የፈጸመው ክህደት ታሪክ የማይረሳው ነው ያሉት ደግሞ ሻምበል ባሻ ጤናው አበበ ናቸው።

ቡድኑ ሲመራውና ሲያስተዳድረው በኖረው ሕዝብ ላይ እንደዚህ አይነት የጭካኔ ተግባር በመፈጸም ታሪካዊ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር በግንባር እያደረገ ያለው ተጋድሎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ሻምበል ባሻ ጤናው ሕዝቡ የአገሩን አንድነትና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ እያደረገ ያለውን ርብርብ ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል አገር ወዳድነቱን በተግባር ማስመስከር እንዳለበትም አሳስበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም