የእሁድ ገበያ በድሬዳዋ እና በአምስት ክልሎች በተመረጡ ከተሞች ሊጀመር ነው

84

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 06/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ተግባራዊ ሆኖ ውጤት የታየበት የእሁድ ገበያ በድሬዳዋ እና በአምስት ክልሎች በተመረጡ ከተሞች ሊጀመር ነው።

በአዲስ አበባ በህብረት ስራ ማህበራት የተጀመረውን የእሁድ ገበያ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አምራችና ሸማች እንዲሁም የህብረት ስራ ማህበራት የተሳተፉበት መድረክ ተካሂዷል።

የህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ሙመድ፤ በከተሞች የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ የህብረት ስራ ማህበራት ምርቶችን በተመጣጠነ ዋጋ ለሸማቾች በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ በህብረት ስራ ማህበራት የተጀመረው የእሁድ ገበያ በዚህ ዙሪያ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው አምራችና ሸማቹን በማገናኘት እንዲሁም የሶስተኛ ወገንን ጣልቃገብነትን ማስቀረት ችሏል ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን መልካም ጀምር በድሬደዋ እና በአምስት ክልሎች በተመረጡ ከተሞች ግብይቱ ይጀመራል ብለዋል።

በኮሚሽኑ የህብረት ስራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው፤ በአዲስ አበባ የእሁድ ገበያን ይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር ዘጠኝ ተጨማሪ ቦታዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

በክልሎችም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሲዳማ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ የተመረጡ አካባቢዎች የእሁድ ገበያ ይጀመራል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ  ጃንጥራር አባይ፤ በከተማዋ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት አስተዳደሩ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ 1 ቢሊዮን ብር መድቦ ለሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ማቅረቡን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ በተመረጡ  11 ቦታዎች የእሁድ ገበያ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ይበልጥ እየተጠናከረ እና እየሰፋ ይሄዳል ብለዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ማዕከል በአጭር ጊዜ መገንባቱን አስታውሰው በቀጣይ መሰል የገበያ ማዕከላትን በየካ፣ ለሚኩራ እና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች ለመገንባት የሚያስችል ጥናት አጠናቋል  ነው ያሉት።

እስካሁን ለሰባት ሳምንታት በተደረገው የእሁድ ገበያ ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈፀሙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም