ግብራችንን በወቅቱ በመክፈል ለህልውና ዘመቻው የኋላ ደጀንነታችንን እናረጋግጣለን

199

ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 6/2014 —ለህልውና ዘመቻው ያለንን ተሳትፎ ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ግብራችንን በወቅቱ በመክፈል የኋላ ደጀንነታችንን እናረጋግጣለን ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ገለፁ።

አሸባሪው ህወሀት በከፈተው ጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም ተገቢውን ግብር መሰብሰብ እንደ አንድ ግብ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ  አስታውቋል።


የከተማ አስተዳደሩ በገቢ አሰባሰብ ስርአቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከከፍተኛ ግብር ከፋይ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል አቶ አለማየሁ ይሁኔ ለኢዜአ እንደገለጹት “የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ ለመከላከያ ሠራዊት ከማደርገው የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ግብሬን በወቅቱ በመክፈል ተሳትፎየንና የኋላ ደጀንነቴን አረጋግጣለሁ” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የውስጥና የውጭ ጫና ለመቋቋም የንግዱ ማህበረሰብ ትልቅ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።

“የማንም ቀስቃሽ ሳያስፈልገን ከወትሮው በተለየ መንገድ ግብርን በወቅቱና በተሻለ ሁኔታ ከፍለን ለአገርና ህዝብ ታማኝነታችንን የምናሳይበት ወቅት ላይ ነን” ሲሉም አክለዋል።

በባህር ዳር ከተማ በዶሮ ርባታና እንስሳት መኖ ንግድ የተሰማሩት አቶ አንዳርጌ አለማየሁ በበኩላቸው ለህልውና ዘመቻው 50 ሺህ ብር በመለገስ አስተዋጾ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

“የንግዱ ማህበረሰብ አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ግብራችንን በወቅቱ በመክፈል አገራዊ ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ግብርን በአግባቡ አለመክፈል አገርን እንደመክዳት ይቆጠራል” ያሉት አቶ አንዳርጌ፣ “የውስጥና የውጭ ጫናውን ለመቋቋም የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅብንን መወጣት ይኖርብናል” ሲሉም አክለዋል።

ነጋዴውም ሆነ ተገልጋዩ ማህበረሰብ  ህጋዊ የደረሰኝ ግብይት በመፈፀም ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙሉዓለም ተፈራ በበኩላቸው በከተማው በክልሉ ወረራ የተፈፀመባቸው አካባቢዎች ገቢን ማካካስ የሚያስችል የግብር አሰባሰብ ሂደት እየተከናወነ ነው።

በተያዘው በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመው ባለፉት ወራት ብቻ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አመልክተዋል።

ክንውኑ ከእዚህ ቀደም በተመሳሳይ ወቅት ይሰበሰብ ከነበረው የተሻለ መሆኑን አቶ ሙሉዓለም ጠቅሰዋል።

“የንግዱ ህብረተሰብ አገሪቱ በህልውና ጦርነት ላይ መሆኗን በመረዳት ተሳትፎው እያደገ መምጣቱ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ አስችሏል ” ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


የህልውና ዘመቻውን በብቃት ለመመከትና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም ተገቢውን ግብር መሰብሰብ እንደ አንድ ግንባር ተደርጎ በትኩረት እየተሰራ ነው” ያሉት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ፀጋ ጥበቡ ናቸው።


በክልሉ በአሸባሪው ቡድን ወረራ ባልተፈፀመባቸው አካባቢዎች ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የህልውና ዘመቻውን መቋቋም የሚያስችል ገቢ ለመሰብሰብ ማህብረሰቡ በግብይትና በአገልግሎት ወቅት ደረሰኝ በመቀበል የኋላ ደጀንነቱን እንዲያጠናክር አስገንዝበዋል።

“በማንኛውም ሁኔታ ግብርን ለማጭበርበር የሚደረገን ጥረት መንግስት አይታገስም” ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አመልክተዋል።

“በአቅጣጫው የተያዙ ተግባራትን ለማከናወን በዋናነት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው” ብለዋል ።

የንግዱ ማህበረሰብ በህልውና ዘመቻው ያደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በገቢ አሰባሰብ በመድገም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይት መድረኩ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ከፍተኛ ግብር ከፋዮችና በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተሳትፈዋል።