የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ድጋፉን እንደሚያጠናክር የጋምቤላ ክልል አስታወቀ

183

ባሀር ዳር ፤ ታህሳስ 6/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች ከጊዜያዊ ድጋፍ ባለፈ መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ እገዛውን እንደሚያጠናክር የጋምቤላ ክልል የተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ።

ከጋምቤላ ክልል ነዎሪዎች የተሰባሰበ የምግብ እህል፣ አልባሳትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች አሸባሪው ቡድን በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ተደርጓል።

በባህር ዳር ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት የኮሚቴ ፀሐፊ አቶ አሊ ኢሳ እንዳሉት፤አሸባሪው የህወሃት ቡድን በከፈተው ጦርነት የተጎዱ ወገኖችን ከጎናቸው በመሆን መደገፍና መተባበር ይገባል።

ኮሚቴውም ከህዝቡ ድጋፍ በማሰባሰብ በአማራና አፋር ክልሎች በሽብር ቡድን ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማገዝ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ በአማራ ክልል ዘንዘልማና እብናት መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች 800 ሺህ ብር ወጪ የተደረገበት የአይነት ድጋፍ አስረክበዋል።

በተጨማሪም 38 ኩንታል የተለያዩ ዓይነት አልባሳትንም ለግሰዋል።

ድጋፉ የተፈናቃይ ወገኖችን ጊዜያዊ ችግር ለመጋራት ያግዛል ያሉት ፀሐፊው፤ በቀጣይም መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ እገዛው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ኮሚቴው ቀደም ሲል በደብረ ብረሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖችም ሦስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማደረጉን አስታውሰው፤ በአፋር ክልል ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች 250 ሺህ ብር በቅርቡ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማገዝ እየተደረገ ያለው ርብርብ የሚያበረታታ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ናቸው።

በጋምቤላ ክልል የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች አጋርነታቸውን ለማሳየት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በአሸባሪው ቡድን በርካታ ህዝብ ለችግር መጋለጡን ገልጸው፤ በመልሶ ማቋቋም ሂደትም ደጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ባለፈው ሳምንት 3 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና አልባሳት በባህር ዳር ከተማ በመገኘት ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።