ኢንስቲትዮቱ የበቆሎ መፈልፊያ ማሽንና የቡና ገለፈትን ወደ ማዳበሪያነት የሚቀይሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ ሊውሉ ነው

100

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 06/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት፤ የበቆሎ መፈልፊያ ማሽንና የቡና ገለፈትን ወደ ማዳበሪያነት የሚቀይሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ ለማዋል እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ፤ ኢንስቲትዩቱ የጤና፣ የግብርና፣ የፋርማሲ፣ የአካባቢ ጥበቃና ሌሎችን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለህብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁንም አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከመፍጠር በተጨማሪ በሌሎች አገራት የተሰሩትን ቴክኖሎጂዎች ወደ ኢትዮጵያ የማላመድ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በቀጣይ ከሚያስተዋውቃቸው ፈጠራዎች መካከል የበቆሎ መፈልፊያ ማሽንና የቡና ገለፈትን ወደ ማዳበሪያነት የሚቀይሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የበቆሎ መፈልፈያው በጅማ ዞን በቆሎ አብቃይ አካባቢዎች ለሕብረተሰቡ ለማስተዋወቅ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በመቀጠልም በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም በቆሎ አብቃይ አካባቢዎች ተመሳሳይ ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

'ቨርሚ ኮምፖስት' የተባለ የቡናን ገለፈት ወደ ማዳበሪያነት የሚቀይር አዲስ የቴክኖሎጂ ውጤት ይፋ የሚደረግ መሆኑንም ዶክተር ካሳሁን ገልጸዋል።

አዲሱን ቴክኖሎጂ አሁን ላይ በቡኖ በደሌ ጮራ በሚባል ወረዳ 20 ወጣቶች እየሰሩበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከግብርና ዘርፍ በተጨማሪ ለጤናው የሚያገልግሉ በቤተ ሙከራ ደረጃ ያሉ ለ'ፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ' ግብዓት የሚውሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሂደት ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

እነዚህ ምርቶች ከውጭ ይገቡ የነበሩ በመሆናቸው በአገር ውስጥ ማምረት መጀመሩ የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ያስችላል ብለዋል።

የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በቀጣይ ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌሎች አገራት ትልቅ ገቢ የሚያስገኘውና መቀንጨርን ለማከም የሚውለውን "ማይክሮ አልጌ"  ለመጠቀም እየሰራ ሲሆን ወደ ውጭ በመላክ ገቢ ለማግኘትም እቅድ እንዳለ ጠቁመዋል።

'ማይክሮ አልጌ' ኢትዮጵያ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ አቢጃታ፣ ሻላ እና ጪቱ የሚባሉ ሃይቆች ላይ በስፋት እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በኢንስቲትዩቱ ቤተ ሙከራ ሌሎች ምርምሮችም እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም