አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማት የምዕራባዊያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ማስፈፀሚያ እየሆኑ መጥተዋል

93

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 06/2014(ኢዜአ) አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማት የምዕራባዊያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ማስፈፀሚያ እየሆኑ መምጣታቸውን በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ኃይሌ ሙሉቀን ገለፁ።

ኢትዮጵያ ይህን ተገቢ ያልሆነ አካሄድ በመቃወም ረገድ የጀመረችውን ጥረት መላ አፍሪካዊያን ሊደግፉት እንደሚገባ ነው ምሁሩ የተናገሩት ።

ዶክተር ሀይሌ ሙሉቀን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በቅኝ ግዛት ወቅት የነበረው ዓለም አቀፋዊ ሁነት አሁን መልኩን ቀይሮ ድጋሚ ወደ አፍሪካ እየመጣ ነው፡፡

የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች በአሁኑ ወቅት በተቋማዊ አገዛዝ የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለመበዝበዝ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አንፃር አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማት የምዕራባዊያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ፍላጎት ማስፈፀሚያ እየሆኑ ስለመምጣታቸው ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ተቋማት ምዕራባዊያኑ የማይፈልጓቸውን መሪዎች ስም ለማጠልሸትና ለማስወገድ እያገለገሉ መሆኑ በግልጽ እየታየ መምጣቱንም ነው ያነሱት፡፡

ለአብነትም "ዩናይትድ ኔሽን ዋር ክራይም ኮሚሽን" ተብሎ የሚታወቀው ድርጅት ኢትዮጵያ ፋሽስት ጣሊያን ያደረሰባትን በደል በሚመለከት ያቀረበችውን ክስ ለመቀበል እንኳን ፈቃደኛ እንዳልነበረ አስታውሰዋል፡፡

ዛሬም የዚህ ድርጅት ተተኪ የሆነው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለአፍሪካውያን ብቻ የተቋቋመ እስኪመስል ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እያገለገለ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል እንዳልሆነች የተናገሩት ዶክተር ኃይሌ፤ ሌሎች አባል የሆኑ የአፍሪካ አገራት ከአባልነት መውጣት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

ኢትዮጵያ ነፃነቷን በማስጠበቅ ለጥቁር ህዝቦች አርዓያ እንደሆነች ሁሉ አሁንም የምዕራባዊያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ማስፈፀሚያ የሆኑ የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጫና በመቋቋም ተምሳሌትነቷን እንደምታስቀጥል ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል፡፡

አፍሪካ ያላትን ሃብት በመጠቀም በዓለም ላይ ያለውን የኃይል ሚዛን መቀየር የሚያስችል አቅም እንዳላት የገለፁት ዶክተር ኃይሌ፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ አፍሪካዊያን ምሁራን በአህጉር ደረጃ ማሰብ አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ምሁራን አፍሪካ ያላትን አቅም በማውጣት ሕዝቦችዋ ወደ መተባበርና መተሳሰር እንዲመጡ በሚያደርጉ ስራዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተው፤ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት መታገል ይገባል ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻር የተባበሩት መንግስታት የፀጥው ምክር ቤት ራሱን ሊፈትሽ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም