በመንግስታቱ ድርጅት የተለያዩ አገሮች የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ለተፈናቀሉ ወገኖች የ55 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረጉ

64

ታህሳስ 6/2014/ኢዜአ/ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ አገሮች የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የ55 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረጉ።

በደቡብ ሱዳን የዩኤን ስታፍና የድጋፉ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮናስ ሰካታ፤ በድርጅቱ የተለያዩ አገሮች ከሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፉ ተሰባስቦ መንግስት ወደ ከፈተው አካውንት ገቢ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለመልሶ ማቋቋሚያ የሚውል 55 ሺህ ዶላር ገቢ መደረጉን ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ዘረፋና ወድመት ማድረሱን ጠቅሰው ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሁላችንም ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎች አሁን ላይ ከወራሪው ነፃ በወጡ አካባቢዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ በማድረግ የዳያስፖራው እገዛ ወሳኝ መሆኑን አቶ ዮናስ ተናግረዋል።

ለዚህም እገዛ የሚሆን ኢትዮጵያዊያን የዩኤን ሰራተኞችን በማስተባበር በአምስት ቀናት ብቻ የ55 ሺህ ዶላር ድጋፍ መሰብሰቡን ጠቁመው በቀጣይም ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት በደቡብ ሱዳን፣ በኡጋንዳ፣ በማእከላዊ አፍሪካ፣ በማሊ፣ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በሃይቲ እና ፉጂ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸውን ለመደገፍና ለአገራቸው መከታ መሆናቸውን በተግባር ማሳየታቸውን የድጋፉ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተናግረዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የተለያዩ አገሮች የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ወርሃዊ ቋሚ ድጋፍ  ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም