በአሸባሪው ሕወሓት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የፊታችን እሁድ ይካሄዳል

70

ታህሳስ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ሕወሓት የወደሙና የተዘረፉ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ የሚውል ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የፊታችን እሁድ ታህሳስ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

መርሃ ግብሩ ያዘጋጁት ግሎባል ኤድ ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክስናስ)፣ የአሜሪካ ኢትዮጵያ ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ፣ የኢትዮ-አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤትና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ነው።

ኢክስናስ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእርዳታ የተለገሱ የጤና ቁሳቁሶችን የሚያሳባስበው ‘ፕሮጀክት ኪዩር’ የተሰኘው ሰብአዊ ድርጅት የተገኙ 18 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ለትራንስፖርትና ማከማቻ የሚያስፈልገውን አንድ ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።

በመሆኑም ይህንን ገንዘብ ለማግኘት ገቢ የማሰባሰብ መርሃ ግብሩ እንደሚካሄድ ገልጿል።

በ50 ኮንቴነር የሚላከው ድጋፍ የሕክምና አልጋዎች፣ ለድንገተኛ ሕክምና የሚያስፈልጉ የጤና ቁሳቁሶችና ሌሎች የሕክምና መገልገያ እቃዎች የያዘ መሆኑ ተጠቅሷል።

የህክምና ቁሳቁሱ ድጋፍ እንዲገኝ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን የጤና ባለሙያዎች፣ አገር ወዳድ ግለሰቦችና የኢትዮጵያ ወዳጆች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ነው ኢክናስ ያስታወቀው።

የሕክምና ቁሳቁሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ውድመትና ዘረፋ ወደ ደረሰባቸው የጤና ተቋማት የማድረስ ስራ እንደሚከናወን ተጠቅሷል።

ከዚህ በፊት ከፕሮጀክት ኪዩር በተገኘ ድጋፍ አምስት ኮንቴነር የህክምና ቁሳቁስ ለደባርቅ፣ ደብረታቦር፣ ጋይንት፣ ነፋስ መውጫ፣ ፈለገ ህይወት፣ ጦር ሃይሎችና የጀግኖች አምባ ሆስፒታሎች ድጋፍ መደረጉን ይታወሳል።

የሕክምና ቁሳቁሶችን የያዙ ሁለት ኮንቴነሮች በአሁኑ ሰአት ወደ ኢትዮጵያ እየተጓጓዙ መሆኑንና የጤና ድጋፉ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ኢክናስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በአሸባሪው ሕወሓት ውድመትና ዘረፋ ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት መልሶ መቋቋም ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

በገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ ላይ ውድመትና ዝርፊያ የደረሰባቸው የጤና ተቋማት በዘላቂነት መደገፍና መርዳት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ዳያስፖራዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ዘረፋና ውድመት እስካሁን ከ2 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንደማይሰጡና በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎች ሲካተቱ ውድመት የደረሰባቸዉ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም