ወተር ኤይድ ኢትዮጵያ መንግስት የንጹህ መጠጥ ውሃን ተደራሽነት ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ

168

ጎባ፣ ታህሳስ 6/2014 (ኢዜአ) ወተር ኤይድ-ኢትዮጵያ መንግስት የንጹህ መጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን  ገለጸ፡፡

ተቋሙ በባሌ ዞን በርበሬ ወረዳ ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለሚያስገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የስራ ማስጀመሪያ ውይይት በጎባ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ያእቆብ መተና እንደተናገሩት  ወተር ኤይድኢትዮጵያ በአገሪቱ ባሉ ከተሞች የውሃ አገልግሎትን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።”

በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ስርዓትን ለማሻሻል የሚረዱ 14 የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በበርበሬ ወረዳ የሚገነባው የውሃ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በሰባት ቀበሌዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር  ከ41 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከእንግሊዝ መንግስት የተገኘ ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን ጠቁመው፤ የግንባታ ስራው በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ጊዜ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል ።

የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለሁሉም ማህበረሰብ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት በመንግስት  ብቻ ማሳካት የማይቻል በመሆኑ የልማት ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ የልማት ድርጅቶች ዳይሬክተር  አቶ ይርዳው ነጋሽ ናቸው፡፡

በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች በወተር-ኤይድኢትዮጵያ  አራት የውሃ ፕሮጀክቶችን እየተገነቡ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ከበርበሬ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ገዛል ሁሴን በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግራቸውን ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማህበረሰቡ የሚጠበቅበትን ሁሉ ይወጣል ያሉት ደግሞ  የወረዳው ነዋሪ አቶ መሐመድ ሹክሪ አብዱላሂ ናቸው፡፡

ወተር ኤይድኢትዮጵያ የውሃ፣ ንጽህናና የጽዳት ፕሮግራሞችን በመቅረጽ የከተሞችን የውሃ አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና የማህበረሰቡን የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ አስቀምጦ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡