ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል ተደራሽ እንዲሆን ጥሪ ቀረበ

90

አዲስ አበባ ታህሳስ 06/2014(ኢዜአ) ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ድጋፉን በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል ተደራሽ በማድረግ እንዲተባበሩ ኮሚሽኑ ጥሪ አቀረበ።

የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመታደግ እየተደረገ ያለው የሃብት ማሰባሰብና ድጋፍ እጅግ የሚበረታታ ቢሆንም በተበታተነ መልኩ መሆኑ ግን ድጋፉ በተገቢው መልኩ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ክፍተት ፈጥሯል፡፡

በተጨማሪም ድጋፉ በተቀናጀ መልኩ ተደራሽ አለመሆኑ ደግሞ ከፍተኛ የሃብት ብክነት እንዲፈጠር ማድረጉንም ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሸባሪው የህውሃት ቡድን ወረራ በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አንሰተዋል።

ይህንን ተከትሎ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ግዜ ምላሽ ማዕከላትን በማቋቋም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

በተጨማሪ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ዜጎች በመደገፍ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ባለኃብቶች፣ታዋቂ ሰዎችና ግለሰቦች በተለያየ መልኩ ተፈናቃይ ዜጎችን እየረዱ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ እጅግ የሚበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የድጋፍ አሰጣጥ ሂደቱ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ባለመሆኑ ድጋፉ በተገቢው መልኩ ተደራሽ እንዳይሆን አድርጓል ይላሉ።

በተበታተነ መልኩ መሰጠቱ ድግግሞሽ እንዲኖር ከማድረጉ ባሻገር ለከፍተኛ የሃብት ብክነት መፈጠር በር ከፍቷል ነው ያሉት።

በተለይ እርዳታው በሚሰጥበት ስፍራ እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው መውሰድ የማይችሉ ዜጎች ለከፍተኛ ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህንን በመገንዘብ ድጋፍ ሰጪ አካላት የሚያስፈልገውን የግብአት አይነት እና የስርጭት ሁኔታን በሚመለከት ከኮሚሽኑ ጋር መረጃን በመለዋወጥ በቅንጅት ለመስራት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

በዋናነት የድጋፍ አሰጣጥ ሂደቱ በአንድ ማእከል እንዲመራ ለማስቻል በኮሚሽኑ በኩል ቢያልፍ የተሻለ ይሆናል ሲሉ ዳይሬክተሩ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

ይህም በመንግስት፣በድጋፍ ሰጪ አካላትና በተፈናቃይ ወገኖች መካከል ያለውን መተማመን ያጠነክረዋል ነው ያሉት።

የመልሶ ማቋቋም ስራው ከፍተኛ በጀትን የሚጠይቅ በመሆኑ የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በድጋፍ ስራው ላይ ጎልቶ የታየው ይህ መነቃቃትና የመረዳዳት መንፈስ በቀጣይም በመልሶ ማቋቋም ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።

በአሸባሪው ህውሃት ወረራ ምክንያት በሚሊዬን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም