ጠላትን እየተዋጋን የልማት ድሎችን ለማስመዝገብ እየሰራን ነው

104

ባህርዳር ፤ታህሳስ 5/2014(ኢዜአ) ጠላትን እየተዋጋን የልማት ድሎችን ለማስመዝገብ አቅጣጫ አስቀምጠን እየሰራን ነው ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን አስታወቁ።

የክልሉ የ2014 የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የንቅናቄ  መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የክላስተሩ አስተባባሪ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህውሃት ቡድን ሀገር የማውደም ግብ ይዞ ተንቀሳቅሷል።

በአማራና አፋር ክልሎች   ወረራ በመፈጸም ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት እያደረሰ ያለውም ያልተረጋጋችና የፈረሰች ሀገር ለማድረግ   እንደሆነ ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታትም በአንድ እጃችን ጠላትን እየተዋጋን በሌላኛው  የልማት ድሎችን የምናስመዘግብበት  አቅጣጫ በማስቀመጥ እየሰራን እንገኛለን ነው ያሉት።

ጦርነቱ ቁሳዊና ሰብአዊ ሃብትን ከማውደሙ ጋር ተያይዞ በጤና ስርዓቱ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስም  አስተማማኝ የጤና መድህን ስርዓት መገንባት አማራጭ እንደሌለው አቶ ስዩም ገልጸዋል።

ለዚህም የክልሉ መንግስት ከዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጤና መድህንን ተደራሽ በማድረግ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የጤና ስርዓት ለመገንባት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የጤና መድህን ህብረተሰቡ ቀድሞ በሚቆጥበው ገንዘብ የጤና ችግር ሲገጥመው ወደ ጤና ተቋም ሂዶ የሚታከምበት አዋጭ ስርዓት ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ናቸው።

ከህብረተሰቡ በሚሰበሰበው ገንዘብም የጤና ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ፣ የህክምና ቁሳቁስ በማሟላት፣ የመድሃኒትና ሌሎች ግብአቶችን በማቅረብ  አገልግሎቱን ፈጣን፣ ተደራሽና ጥራት ያለው እንዲሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።

እንደ ዶክተር መልካሙ ገለጻ፤  ከአስር ዓመት በፊት በክልሉ በሶስት ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አሁን ላይ በሁሉም ወረዳዎች ተደራሽ በማድረግ ከክልሉ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

ባለፈው ዓመት አባላት ተጨማሪ በማፍራትና ሃብት በማሰባሰብ ከቀዳሚው ዓመት ከነበረው 57 በመቶ ወደ 67 በመቶ ማሳደግ መቻሉ በዚህ ዓመትም በችግር ውስጥ ሆነን ከዚህ በላይ እንድናስመዘግብ ተነሳሽነትን ይፈጥሯል ነው ያሉት።

በንቅናቄው መድረክ የተገኙት የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ በ834 ወረዳዎች ከ8 ነጥብ ሰባት ሚሊየን በላይ አባውራዎችና እማውራዎች የመድህኑ አባል መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥም ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ያህሉ በአማራ ክልል የሚገኝ በመሆኑ በቁጥር ብዛት፣ በአጀማመር፣ በውጤታማነትና ከተጠቃሚነት አንጻር ግንባር ቀደም መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ  በክልሉ የተካሄደው  የንቅናቄ መድረክ በእልህና በወኔ የምናካሂደው በዓይነቱ ለየት ያለ ነው  ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ፤ ይህም አሸባሪው ህሀሃት ያደረሰውን ጉዳት በሚያካክስ መልኩ እንደሚተገበር ተናግረዋል።

የጤና መድህን ስርዓቱን ማስቀጠል ከህልውና ትግሉ ባልተናነሰ መልኩ የሚፈጸም በመሆኑ በቀጣይ በወረራ ውስጥ በቆዩ ወረዳዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን አስገዳጅ የጤና አቅርቦት ለማሟላት የሚያስችል ተመራጭ ስርዓት በመሆኑ የአመራሩ ትኩረት እንደማይለየው ተመልክቷል።

በንቅናቄው መድረክ በምዕራብ አማራ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች  የተወጣጡ የጤና መምሪያ ሃላፊዎች እና የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከታቀፉ ዜጎች ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ከጤና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም