አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባት ጭፍራ ከተማ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል

225

ታህሳስ 5/2014/ኢዜአ/ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን በወረራ በቆየባት ጭፍራ ከተማ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን የጭፍራ ወረዳ አስተዳዳሪ ቢቲካ ኑሪ ገለጹ ።

አሸባሪው ህወሃት በአማራና የአፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ከግለሰብ ጓዳ አንስቶ እስከ መንግስትና ህዝብ ንብረቶች ዘረፋና ወድመት ፈፅሟል።

በዚህም በርካታ የወረዳው ነዋሪዎች ለከፋ ችግርና እንግልት መዳረጋቸውን የጭፍራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢቲካ ኑሪ ተናግረዋል።

በንግድና በሞቀ የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ትታወቅ የነበረችውን ጭፍራ ከተማ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟባታል ብለዋል።

አሸባሪው ሃይል በጭፍራ ከተማ ካደረሰው ወድመት በተጨማሪ የአርሶና አርብቶ አደር እንስሳትን የተመረዘ ምግብ በመስጠት መግደሉን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት ካደረሰው ጥፋት ለማገገም የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ በማውጣት ይሰራል ያሉት የወረዳ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን መልሶ ለማቋቋምና ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

በመልሶ ማቋቋምና የግንባታ ስራ መላ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በአሸባሪው ህወሃት ከወረዳዋ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል።