በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናት በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው

208

ታህሳስ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናት በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የሆነ ቁሳዊና ሰብዓዊ ውድመት አድርሷል።

በሴቶችን ህጻናት ላይ አስገድዶ የመድፈር ጥቃትን ጨምሮ እጅግ አሰቃቂ ግፍ የፈጸመ ሲሆን፤ በርካታ ዜጎች ደግሞ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች  የህዝብ መገልገያ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙ ደግሞ ችግሩን እንዲባባስ አድርጓል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአሸባሪ ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም ሃብት የሚያሰባስብ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል፡፡

ግብረ-ሃይሉ በተለይ በአሸባሪ ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናትን ለመደገፍ እንደሚሰራም ነው ያነሱት፡፡

ህብረተሰቡ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የእለት ደራሽ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ድጋፉም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ከቀዬአቸው የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ባለድርሻ ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዜጎችን መልሶ የማቋቋሙ ስራ በመንግስት ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸው፤ በተለይ በጎ ፈቃደኞች የወደሙ መኖሪያ ቤቶችን መልሶ በመገንባት ተግባር እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት የመልሶ ማቋቋም መርሃ-ግብር እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሽብር ቡድኑ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናትን የስነ-ልቦና ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡ 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።