አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚያደርሰውን ግፍና መከራ የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሄዱ

197

ሆሳዕና/ዲላ ታህሳስ 5/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸመውን ግፍና መከራ የሚያወግዙ ሰልፎች ዛሬ በደቡብ ክልል ከምባታ ጠምባሮና የጌዴኦ ዞኖች ተካሄዱ።

ሴቶቹ ባደረጓቸው ሰልፎች አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች በሴቶችና ህጻናት ላይ እየፈጸመው ያለውን ግፍና በደል አጥብቀው ተቃውመዋል።

በዱራሜ በተካሄደው ሰልፍ የተሳተፈችው የሂጋ ሞዴል  አዳሪ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሜሮን ተመስገን  አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች በሴቶችና ህፃናት ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ግፍና መከራ እንደምትቃወም ገልጻለች።

”ሴት የሀገር መሪን የምትወልድና ለሀገር መሠረት ነች” ያለችው ተማሪ ሜሮን ፤በሴቶችና ህፃናት ላይ እየተፈፀመ የሚገኘው በደልና ግፍ መብቃት አለበት ብላለች።

አሸባሪው ቡድን በሴቶችና በህጻናት ላይ እያደረሰ ያለውን  ግፍ  እንዲያቆም ድምጻቸውን ለማሰማት በሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ መምሪያ ባለሙያ ወይዘሮ ራሄል አበራ ናቸው።

የከምባታ ጠምባሮ ዞን የሴቶች ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ምህረት ዮሴፍ  አሸባሪው ህወሃት  በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በጤና ተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመት ቅድሚያ ተጎጂዎቹ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

በተመሳሳይ በጌዴኦ ዞን በተካሄደው ሰልፍ ከተሳተፉት መካከል  የይርጋጨፌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ፀጋነሽ ሃይሉ ፤አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በተለይ በሴቶች፣ በእናቶችና ህጻናት ላይ የፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት ለመቃወም በሰልፉ መሳተፏን ገልጻለች።

አሸባሪው ቡድን በዜጎች ላይ የፈጸማቸው ወንጀሎች ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ ናቸው ያለችው ፀጋነሽ፤ አሸባሪው ቡድን በፈጸመው ግፍና በደል በዓለም አቀፍ ሕግ መጠየቅ  አለበት ብላለች።

”ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች በቆዬባቸው ጊዜያት የግፍ በትሩን ያሳረፈባቸው ሴቶች ድምጽ ከመሆን ባለፈ ልንደግፋቸው ይገባል” ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ አልማዝ በራሶ ናቸው።

ቡድኑ ሴቶችን ከመድፈርና ከማሰቃየት ባለፈ  ህብረተሰቡ የሚገለገልባቸውን ተቋማት በመዝረፍና በማውደም የፈጸማቸው ወንጀሎችን አጥብቀው ኮንነዋል።

የይርጋጨፈ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ውበት ድንቢ በበኩላቸው፤ የወረዳው ሴቶች አሸባሪው ቡድን በሴቶችና በህጻናት ላይ የፈጸመውን አስነዋሪ ተግባር ማውገዛቸው ተገቢና ትክክለኛ  መሆኑን አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሓት በደረሰባቸው አካባቢዎች መነኩሳትን ጨምሮ እናቶችንና ህጻናትን በመድፈር ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸሙ ይታወቃል።

በተጨማሪም ህጻናትን በውትድርናና በጉልበት ሥራዎች በግዳጅ በማሰማራት ግፍና በደል ሲፈጽም መቆየቱን የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ያመላክታሉ።