አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ ወደ አገር ቤት ሲመለስ ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል-ኮሚቴው

917

አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ ወደ አገር ቤት ሲመለስ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግለት የዝግጅት ኮሚቴው አስታወቀ።

ኮሚቴው ታማኝ በየነ  ከ27 አመት በኋላ ወደ አገር ቤት ሲመጣ የሚደረግለትን አቀባበል አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ነሐሴ 26 ወደ አገር ቤት ሲመጣ አድናቂዎቹ፣ አርቲስቶችና ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች አቀባበል ያደርጉለታል።

በእዕለቱም ታማኝ ኢትጵጵያ ሲደርስ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መግለጫ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል።

በመቀጠልም የሙያ አጋሮቹ በብሄራዊ ትያትር ልዩ ዝግጅት በማድረግ አቀባበል እንደሚያደርጉለትም ተገልጿል።

ነሐሴ 27 ከሰዓት በኋላ በሚሊኒየም አዳራሽ አድናቂዎቹ፣ የሙያ አጋሮቹና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው አንግዶች በሚገኙበት ሰፊ ፕሮግራም እንደሚደረግለትም ኮሚቴው አስታውቋል።

ለዚህም የመጥሪያ ካርድ በከተማው በሚገኙ ትያትር ቤቶች፣ የወረዳ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጽህፈት ቤቶችና በአንዳንድ ሆቴሎች እንደሚሸጥም ተገልጿል።

የሰላምና የአንድነት አቀንቃኙ ታማኝ በየነ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞችም በመዘዋወር ከአድናቂዎቹና ከህብረተሰቡ ጋር እንደሚገናኝ ተጠቁሟል።