ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ለተፈናቃይ ወገኖች 15ሺህ ዶላር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

135

ደብረ ብርሃን፤ ታህሳስ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ማህበራዊ ትረስት ፈንድ በአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጊዜዊ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች 15ሺህ ዶላር የሚገመት የአልባሳት ድጋፍ አደረገ።

የአዲስ አበባ ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ድጋፍ ለተፈናቃይ ወገኖች እንዲደርስ ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ደብረ ብርሃን ከተማ በመገኘት አስረክቧል።

የፈንዱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ድጋፉ በአሜሪካን ሎሳንጀለስ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር የተገኘ ነው።

በሎሳንጀለስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ድጋፉን ያሰባሰበው ሃና ፋውንዴሽን የተሰኘ ድርጅት መሆኑንም አመላክተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ እንዳሉት ከኢትዮጵያዊያና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተገኘው በዚሁ የገንዘብ ድጋፍ የተገዙት ብርድ ልብሶች ለተፈናቃይ ወገኖች የሚደርስ ናቸው።

በድጋፉ የተሳተፉትን ሁሉ ወይዘሮ እናትዓለም አመስግነው፤ ለድጋፍ የዋለው ዶላር ለሀገሪቱ ውጭ ምንዛሬ ግኝት ራሱን የቻለ  አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

እንዲሁም ብርድ ልብሶቹ ከሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተገዙ በመሆናቸው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዝውውሩ ውስጥ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ወልደአማኑኤል ድጋፉን ሲረከቡ እንዳሉት፣ አሸባሪው ህወሓት ባደረሰው ጥፋት ንጹሃን ዜጎች ከመፈናቀላቸው በላይ የመሰረተ ልማት አውታሮች ወድመዋል።

ምክትል አስተዳዳሪው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ድጋፉ በቀጥታ ለተጎጂዎች እንደሚደርስ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ከወራሪው ህወሓት ነፃ በወጡ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃይ ወገኖችን ወደ ቄያቸው የመመለስ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም  እየተደረገ ላለው ጥረት ስኬት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ሲሳይ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም