በአሸባሪው ህወሃት ውድመት የደረሰበት የኮምቦልቻ ሰመራ ኤሌክትሪክ ሳይት ጥገና በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ይጠናቀቃል

83

ታህሳስ 5/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ህወሃት ውድመት የደረሰበት የኮምቦልቻ ሰመራ ኤሌክትሪክ ሳይት ጥገና በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ይጠናቀቃል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ከኮምቦልቻ እስከ ሰመራ ባለው ማስተላለፊያ መስመር ላይ 52 ሚሊዮን ብር የሚገመት ውደመት ማድረሱም ተጠቁሟል፡፡

የአሸባሪው ህወሃት ቡድን በአፋርና በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የህዝብና የመንግስት መገልገያ መሰረተ ልማቶችን፣ ተቋማትና ድርጅቶችን እንዲሁም የግለሰብ ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ጸረ-ህዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡

ከኮምቦልቻ ወደ ሰመራ የሚሄደው ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚና አስተላላፊ የኤሌክትሪክ ሳይት ደግሞ በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው መሰረተ ልማቶች አንዱ ነው።

ይህም በሰመራና በተለያዩ የአፋር ክልል ከተሞች በሚኖሩ ዜጎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ለወራት የዘለቀ አሉታዊ ጫና አሳድሮ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ኦፕሬሽን ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ኃብታሙ ውቤ፤ አሸባሪው ህወሃት ወራሪ ኃይል ውድመት ያደረሰባቸውን ከደብረሲና እስከ ደሴ ድረስ የሚገኙ መስመሮችን በመጀመሪያ ምዕራፍ ጥገና ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ከኮምቦልቻ እስከ ሰመራ ባለው ማስተላለፊያ መስመር ላይ 52 ሚሊዮን ብር የሚገመት ውደመት ማድረሱንም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም ሁለት ኃይል ተሸካሚ ታወር እና ኃይል አስተላላፊ ኮንዳክተሮች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን አሁን ላይ ከኮምቦልቻ ሰመራ ያለው ኤሌክትሪክ ሳይት ጥገና ከ60 በመቶ በላይ መጠናቀቁን አመላክተዋል።

ውድመት የደረሰባቸው ጥሬ ዕቃዎች የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ቢሆንም የቅድመ ዝግጅት ስራው ፈጥኖ  በመከናወኑ ወደ ጥገና ስራ መግባት እንደተቻለ ጠቁመዋል።

ከ150 በላይ ሰራተኞችን በመመደብ ጥገናውን በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ከሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይል ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ፈጣን የጥገና ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም