የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አስረከቡ

176

ታህሳስ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያሰባሰቡትን ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስረክበዋል፡፡

ድጋፉን ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የትራንስፖርት ቢሮና ሌሎች በአስተዳደሩ ስር የሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ናቸው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ እንዳሉት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ወጣቶችን፣ አትሌቶችንና የስፖርት ቤተሰቦችን በማስተባበር ከ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የጥሬ ገንዘብና የአይነት ድጋፍ አሰባስቦ አስረክቧል።

ቢሮው ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኘችው አትሌት ጌጤ ዋሚ ”ሀገራችን አሁን ያለችበትን ከባድ ጊዜ እንድታልፍ ሁሉም ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን በመቆም ሰራዊቱንና የተፈናቀሉ ወገኖችን መርዳት ይኖርበታል” ብላለች፡፡

”አሁን ያደረግነው ድጋፍ በቂ አይደለም፤ ድጋፋችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” በማለትም ተናግራለች።

ድጋፉን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተር ፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ድጋፉን ላደረጉት አትሌቶች፣ የስፖርት ቤተሰቦች፣ የመንግስት ተቋማትና የግል ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።

በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ተቋማቱም ሆኑ ባለሃብቶች በመልሶ ግንባታውም ላይ ተሳታፊ በመሆን አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፍ ካደረጉ ተቋማት መካከል የወጣቶችና ስፖርት፣ የትራንስፖርት ቢሮ፣ የከተማዋ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን፣ አንበሳ የከተማ ትራንስፖርትና የእምነት ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ የግል ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።