ኀብረተሰቡ የሕልውና ዘመቻውን ከመደገፍ ጎን ለጎን ደም በመለገስ ያደረገው ተሳትፎ ውጤታማ ነው

55

ታህሳስ 5/2014/ኢዜአ/ ኀብረተሰቡ የሕልውና ዘመቻውን ከመደገፍ ጎን ለጎን ደም በመለገስ ያደረገው ተሳትፎ ውጤታማ መሆኑን የብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ገለፀ።

የብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሐብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም  ጀምሮ በተካሔደው ደም የመሰብሰብ  መርሃ-ግብር ኀብረተሰቡ አበረታች ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ኀብረተሰቡ "ደሜን ለመከላከያ ሰራዊቱ" በሚል የተካሄደውን ደም የመሰብሰብ መርሃ-ግብር የህልውና ዘመቻው አካል በማድረግ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉንም ነው ያነሱት፡፡

በመሆኑም በመላው አገሪቱ ደም ለመሰብሰብ በተካሄደው ዘመቻ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ገልጸው፤ በመርሃ ግብሩ ለተሳተፉ ዜጎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ደም የማሰባሰብ ዘመቻው የኀብረተሰቡን ደም የመለገስ ባህል በማጎልበት ረገድ በጎ ሚና መጫወቱንም ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ  አቶ ሐብታሙ ታዬ ተናግረዋል፡፡

''ደም መስጠት ውድና ታላቅ ስጦታ ነው፤ ነገር ግን የደም አሰባሰቡ ስርዓት የተደራጀና ቀጣይነት ባለው አግባብ እንዲካሔድ ለማድረግ ቀሪ የቤት ስራዎች አሉ'' ነው ያሉት።

ደም በባሕሪው ተከማችቶ የሚቆይበት ጊዜ የተገደበ በመሆኑ ኀብረተሰቡ ይሕን በመገንዘብ በቀጣይነት ደም ለመለገስ ከባንኩ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበትም ነው የተናገሩት፡፡

ከለጋሾች የሚገኘው ደም በተደራጀ አግባብ ካልተመራ ጥቅም ላይ ሳይውል ሊበላሽ እንደሚችል ጠቅሰው፤ በመሆኑም ኀብረተሰቡ የብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ደም ተከማችቶ የሚቆይበት ጊዜ የተገደበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ  "በቂ ደም አለ" ማለት ደም አያስፈልግም ማለት ሳይሆን ለአንድ ወር የሚበቃ ክምችት መኖሩን መግለጽ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

"ደም መለገስ የበጎ አድራጎት ስራ ነው" የሚሉት አቶ ሐብታሙ፤  በየወቅቱ ደም በመለገስ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት መታደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም