በክልሉ ከለማው የዘማች ቤተሰቦች የሰብል ምርት ውስጥ 90 በመቶው ተሰብስቧል

118

ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 5/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ባለፈው የመኸር ወቅት ከለማው የዘማች ቤተሰቦች የሰብል ምርት ውስጥ 90 በመቶው ከማሳ ላይ መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው አመራሮችና ባለሙያዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ ኮንች ቀበሌ ዛሬ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰብስበዋል።

በዚህ ወቅት የቢሮው ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መንግስቱ ድልነሳ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገርን ለማዳን ከክልሉ   ወደ ጦር ግንባር የዘመቱ   ሚሊሻዎች 45 ሺህ 290 ሄክታር መሬት በመኽር ወቅት በተለያየ  ሰብል ለምቷል።

የእነዚህ ዘማች ቤተሰቦች የደረሰ ሰብል ሳይባክን በወቅቱ እንዲሰበሰብ ከክልል እስከ ቀበሌ ህብረተሰቡን የማስተባበርና የማነቃነቅ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮችን፣ የመንግስት ሠራተኞች እና ተማሪዎችን በማሳተፍ በተደረገው ጥረት በወቅቱ ከለማው መሬት  የደረሰ 90 በመቶው የሰብል ምርት ከማሳ ላይ  መሰብሰብ መቻሉን  ገልጸዋል።

የዘማች ቤተሰቦች ሰብል እንዳይባክንና ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፣ ቀሪ ሰብሉንም ህዝቡን በማስተባበር በፍጥነት እንደሚሰበሰብ አስታውቀዋል።

ሀገራቸውን ለማዳንና የህዝባቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ ወደግንባር  የዘመቱ ወገኖች  ሰብል መሰብሰብ የእያንዳንዱ ሰው ሃላፊነት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሰብል ስብሰባው ላይ የተሳተፉት አቶ አበበ ደሴ የተባሉ የቢሮው ሠራተኛ ናቸው።

"የዘማች ቤተሰቦች ሰብል እንዳይባክን ማድረግና ከጎናቸው መቆም እነሱ እየከፈሉት ላለው የህይወት ዋጋ ቢያንስባቸው እንጂ አይበዛባቸውም" ብለዋል።

በይልማና ዴንሳ ወረዳ ኮንች ቀበሌ ሰብላቸው የተሰበሰበላቸው የዘማች ቤተሰብ ወይዘሮ ፋሲካ ታከለ በበኩላቸው፤ ባለቤታቸው ወደ ግንባር ሲሂድ ሰብሉ ላይሰበሰብ ይችላል የሚል ሰጋት ገብቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም   የግብርና ቢሮ ሠራተኞች በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብላቸውን በፍጥነት በመሰብሰባቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ሚሊሻው የህዝብና የሀገር ህልውና ለማስጠበቅ ወደግንባር ሲሄድ መንግስት የዘማቾች ሰብል እንዲሰበሰብ ማድረጉ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የእናምርት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ካሳዬ አለባቸው ናቸው።

አንድ ሄክታር በቆሎና ዳጉሳ በህብረተሰቡ ትብብር እንደተሰበሰበላቸው ገልጸው፣ መንግስት ህዝቡን በማስተባበር ሰብላቸው በወቅቱ እንዲሰበሰብ በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በአማራ ክልል በመኽሩ ወቅት  4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ከለማው ሰብል  እስካሁን 58 በመቶ  መሰብሰቡን ከግብርና ቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም