በክልሉ በሁሉም ግንባሮች የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

58

ሐረር፤ ታህሳስ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) በክልሉ አካባቢን ከመጠበቅ ጀምሮ በሁሉም ግንባሮች የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

የቀድሞ ሰራዊት አባላት ከህብረተሰቡ ጋር አካባቢውን ለመጠበቅ በተዘጋጁበት ወቅት የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ  እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር  የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች የሚችሉትን ሁሉ ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም፤መቼም አይችሉም።

ውጤቱም ዋንኛው  ህብረ ብሔራዊ አንድነት እና በኢትዮጵያዊነት ስሜት መንቀሳቀስ መቻላችን  ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰራዊቱን በግንባር ለመምራት በዘመቱበት ወቅት ጥሪ ከማድረጋቸው በፊት ጀምሮ ለሀገር ህልውና መጠበቅ ክልሉ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

በቀጣይም  በክልሉ  በሁሉም ግንባሮች የምንተገብረውን  ስራ ሁላችንም አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።

ከግንባሮቹም መካከል የሀብት አሰባሰብ፣ የተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ፣ የዘማች  ቤተሰብ እንክብካቤ፣ የስንቅ ዝግጅትና አቅርቦት እንዲሁም የአካባቢ ሰላምና ደህንነት ይገኙበታል።

በክልሉ እነዚህን ለማሳካት የተጀመሩ ተልዕኮችን ከግብ ማድረስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉን ሰላም ከማረጋገጥ አንጻር አካባቢን ከመጠበቅ አኳያ የተጀመሩ አበረታች ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከምልስ የሰራዊቱ አባላት  መካከል ምክትል አስር አለቃ ፍሬዘር ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ ባላቸው ሙያ  በመታገዝ  በሰላም እና ልማት ግንባሮች ላይ በመሰለፍ አስተዋጽኦ ለማደረግ ተዘጋጅተዋል።

እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሽብር ተልዕኮ የሚፈጽሙ አካላትን ተግባር ለማክሸፍ በቅንጅት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም