በኮምቦልቻ የሚገኘው ኤም ኤስ ኤ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በአሸባሪው ህወሃት ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል

102

ታህሳስ 5/2014 /ኢዜአ/ በኮምቦልቻ የሚገኘው ኤም ኤስ ኤ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በአሸባሪው ህወሃት ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል።

ኤም ኤስ ኤ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በየዓመቱ በአማካይ ከ25 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ፋብሪካ ነው።

ከአርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በቀጥታ በመቀበልና የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ በርካቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ፋብሪካው በዓመት 200 ሚሊየን ብር ግብር በመክፈልም ለአገር አስተዋፅኦ እያደረገ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ የአሸባሪው ህወሃት የዘረፋና ወድመት ሰለባ ሆኗል።

የፋብሪካው የጥበቃ ሃላፊ ኢንስፔክተር ሙለታ ሲሳይ፤ አሸባሪው ህወሓት ኮምቦልቻ ከተማን በወረረበት ወቅት ወደ ፋብሪካው በመግባት የቻለውን ዘርፎ ያልቻለውን ደግሞ አውድሞታል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው ቀናት 855 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ንብረት ላይ ዘረፋና ውድመት ማድረሱን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ምስጋናው ተገኘ ተናግረዋል።

ለውጭ ገበያ የተዘጋጀ 26 ሺህ ኩንታል ማሾ፣ የሽንብራና ቦለቄ ምርት ከጥቅም ውጭ ሆኗል ብለዋል።

ከአምባሰል፣ ተሁለደሬና ቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር በሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለውጭ ገበያ ተብሎ የተዘጋጀ ሰብልም በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት ሳይሰበሰብ ቀርቷል ብለዋል።

ቀደም ሲል ለዘርና ሌሎች ግብአቶች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑን አቶ ምስጋናው አስታውሰዋል።

የዚሁ ፋብሪካ እህት ኩባንያ አማር ፒፒ ከረጢት ፋብሪካም የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ዘረፋና ውድመት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሶበታል።

የአማር ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አያሌው፤ የደረሰውን ውድመት በማካካስ ወደ ስራ ለማስገባት የመንግስት ትብብር ያስፈልገናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም