ቱርክ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ ልታጸድቅ ነው

268

ታህሳስ 5 ቀን 2014 ዓ.ም( ኢዜአ) ቱርክ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ ልታጸድቅ መሆኑን የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ረሲብ ጠይብ ኤርዶጋን ተናገሩ፡፡

ህዝባችን ትክክለኛ እና ሚዛናዊ የሆነ መረጃ የማግኘት መብቱን ለማስጠበቅ እየሞከርን ነው ያሉት ፕሬዚደንቱ በተለይም በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ምክንያት ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍላችንን ከሚደርስበት ጉዳት ለመከላከልም ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

አዲሱ ህግ የማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚቆጣጠር ተቋም እንደሚመሰረትም ተናግረዋል፡፡

ሀሰተኛ ዘገባ እና የተሳሳተ መረጃ በሚያሰራጩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እስከ 5 ዓመታት በሚደርስ የእስር ቅጣት የሚያስከትሉ ድንጋጌዎችን ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቱርክ ባለፈው ዓመት ከአንድ ሚሊየን በላይ ተከታይ ያላቸውን የማህበራዊ ሚዲያዎች በሀገሪቱ ወስጥ ህጋዊ ተወካይ እንዲኖራቸው እና የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች በመረጃ ቋት ውስጥ እንዲያስገቡ የሚያስገድድ ህግ አውጥታ ስራ ላይ አውላለች፡፡

የዚህን ህግ መውጣት ተከትሎም እንደ ፌስ ቡክ፣ ቲውተር እና ዩቲዩብ የመሳሰሉት ድርጅቶች በቱርክ ህጋዊ ቢሮ ከፍተው መስራት መጀመራቸው ይታወሳል፡፡