የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳትና ምግቦች የሚተዋወቁበት ባዛርና ኤግዚቢሽን ሊዘጋጅ ነው

209

ታህሳስ 5 /2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳትና ምግቦች ለዳያስፖራና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚተዋወቁበት ባዛርና ኤግዚቢሽን ሊዘጋጅ መሆኑን የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ማህበር ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ለበዓል ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ጥሪውን ተከትሎ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በርካቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም እንግዶቿን ለመቀበል በብዙ መልኩ ዝግጅት በማድረግ “ቤት ለእምቦሳ” እያለች ሲሆን የእንግዶቹ ቆይታ የተሳካና የሚወዱት እንዲሆን መንግስትና የግሉ ዘርፍ ጭምር እየሰሩ ነው።

የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ማህበር፤ ወደ አገር ቤት የተጋበዙትን ዳያስፖራዎች ታሳቢ ያደረገ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳትና ምግቦች የሚተዋወቁበት ባዛርና ኤግዚቢሽን በማሰናዳት ላይ ይገኛል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት አለባቸው ወዳይ፤ ወደ አገር ቤት ለሚመጡ እንግዶቻችን ከአቀባበል ጀምሮ ቆይታቸውን ያማረ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳትና ምግቦች በአደባባይ የሚታዩበት እና ለሌሎችም የሚተዋወቁበት ባዛርና ኤግዚቢሽን እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በማስታወቂያ ማህበሩ በኩል ወደ አገር ቤት ለሚመጡ እንግዶች ሁሉ ” እንኳን ደህና መጣችሁ” በማለት በኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጅት መኖሩንም የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋሻው ተናግረዋል።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለ ኢትዮጵያ ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጩ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆቿ ወደ አገር ቤት መምጣታቸው ልዩ ትርጉም ያለው በመሆኑ እንግዶቻችንን ለመቀበል ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ አቶ አኪያ ተሾመ ናቸው።  

የማህበሩ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሀብታሙ ቦርሶማ፤ በመዲናዋ ያሉ የማስታወቂያ መስቀያ ቢል ቦርዶች የከተማዋን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ ለመቀየር ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት ለመግባት እየተመዘገቡ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።