ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ለመምጣት ከፍተኛ ተነሳሽነት እያሳየ ነው

172

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5/2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ለመምጣት ከፍተኛ ተነሳሽነት እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ዳያስፖራው በአንድ ወር ጊዜ ብቻ በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች የሚውል ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ ገቢ ማድረጉንም ነው ኤጀንሲው የገለጸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በውጭ አገራት የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ -ኢትዮጵያውያን ለመጪው ገና ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ወደ አገር ቤት ሲመጡ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ የውጭ አገር ዜጋ ይዘው እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ግርማ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ጥሪውን ተከትሎ ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት እንዲመጣ ኤጀንሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እቅድ አውጥቶ በቅንጅት እየሰራ ነው፡፡

ጉዳዩን የሚያስተባብር ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸው፤በተለያዩ አገራት ያሉ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት እንዲመጣ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነት በመቃወም የ”#በቃ” ዘመቻ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው፤ የዘመቻው አካል የሆኑ ሰልፎች በ40 የተለያዩ ከተሞች መካሄዳቸውን አንስተዋል፡፡

“አንዳንድ የውጭ አገራት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳልሆነች በማስመሰል ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ጥሪ ሲያቀርቡ እየተሰማ ነው” ያሉት አቶ ወንድወሰን ፤ ከዚህ አኳያ የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣት ትርጉሙ ብዙ ነው ብለዋል።

የዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አንዳንድ የምእራባውያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት መረጃ ትክክል አለመሆኑን እንደሚያጋልጥም ነው የተናገሩት፡፡

ዳያስፖራው ወደ አገሩ ለመምጣት ከፍተኛ ተነሳሽነት እያሳየ መሆኑን ገልጸው፤ በአውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከ200 እስከ 300 በመሆን የቻርተር በረራ እያስፈቀዱ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ዲያስፖራው በምዕራባዊያን ዘንድ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበትን የገና በዓል በኢትዮጵያ ማሳለፉ ደግሞ የአገር ውስጥ ቱሪዝምንና የአገልግሎት ሰጪ ዘርፉን የሚያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው ዳያስፖራው በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቹን የሚደግፍበት “አይዞን ዶት ኮም” የተሰኘ የድረ ገጽ መተግበሪያ ማዘጋጀቱን ገልጸው፤ በተለይ የ”#በቃ” ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ መተግበሪያውን በመጠቀም ድጋፍ የሚያደርጉ የዳያስፖራ አባላት ቁጥር ጨምሯል ነው ያሉት፡፡

ዳያስፖራው በአንድ ወር ጊዜ ብቻ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች የሚውል ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ ገቢ ማድረጉንም ለአብነት አንስተዋል፡፡

ይህም ኤጀንሲው በስድስት ወራት ውስጥ አሰባስበዋለሁ ካለው ገቢ የ30 በመቶ ድርሻ እንዳለው ነው የገለጹት፡፡